ፌዴራል ፖሊስ በወንዶች አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የቦክስ ክለብ ውድድር አሸናፊ ሆኑ

53
ኢዜአ ታህሳስ 11/2012 ፌዴራል ፖሊስ በወንዶች፣ አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የቦክስ ክለቦች ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆኑ። ከታህሳስ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የክለቦቹ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። ፌደራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ የሀድያ ዞን የቦክስ ቡድን፣ የሶማሌ ፖሊስ የቦክስ ቡድን፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጎንደር ከተማና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተሳትፈዋል። በወንዶች ከ52 እስከ ከ91 ኪሎ ግራም በላይ፤ በሴቶች ከ51 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድሩ የተካሄደባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። ዛሬ በውድድሩ ማጠናቀቂያ በ52፣ 57፣ 63፣ 69 እና 75 ኪሎ ግራም ወንዶች እና በ57 ኪሎ ግራም ሴቶች የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄደዋል። በአራት ቀናት አጠቃላይ የድምር ውጤት ፌዴራል ፖሊስ በወንዶች፣ አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የውድድሩ ዓላማ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር በቦክስ ስፖርት ለመሳተፍ እንዲችሉ በየካቲት 2012 ዓ.ም በሴኔጋል በሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ ነው። ለክለቦችም የውድድር አማራጭ ማስፋት ሌላኛው የውደድሩ አላማ እንደነበር ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት ውስጥ አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ቀሪ ሶስት ውድድሮች በጎንደር፣ በወላይታ ሶዶና በአዲስ አበባ ከተሞች እንደሚካሄዱ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ሲሰጥ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ ያሰለጥኑ የነበሩ እንግሊዞች የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ። ስፖርቱን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በ1954 ዓ.ም ተመስርቷል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም