"ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ጊዜ ነው ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች" - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

96
ኢዜአ ታህሳስ 10/2012.. "ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ጊዜ ነው ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። ባለፉት ሳምንታት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ ስራ ሃላፊዎች፣ የንግድ ማኅበረሰብ፣ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አንቂዎች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖትና የማኅበረሰብ አመራር አባላት መካከል ሲካሄድ የቆየው የሰላም ኮንፈረንስ የማጠቃለያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅናና ሽልማት እያገኘች ነው። ዛሬም የመጀመሪያውን ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም "የኢትዮጵያን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርጓል" ብለዋል። በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ ከአጋሮች በሚደረገው ድጋፍና መንግስት ፈሰስ በሚያደርገው በጀት የሚሰራው ስራ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለውጥ እንደሚያስገኝ አመልክተው፤ ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ አምስት ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች አንዷ  እንደሚያደርጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። "ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ጊዜ ነው ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ኢትዮጵያን ከመበልጸግ የሚያቆማት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ አሁን ያሉባትን ፈተናዎችና ችግሮች አልፋ ወደ ብልጽግና እንደምትሸጋገር ገልጸዋል። የሰላም ኮንፍረንሱ ለዘላቂ ሰላም ግንባታው መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመው፤ 'ቀጣይ ብዙ የቤት ስራዎች ይጠብቁናል' ብለዋል። ሰላምን ለማምጣት ቁልፉ መቻቻል መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝቦች ልዩነታቸውን አቻችለው ለሰላም መስፈን መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም