ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንደምትመለስ ጥርጣሬ አይኑራችሁ-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

74
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንድትመለስ መሻገሪያ አቅጣጫዎች ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ይገባል አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርሳቸውን ለመደገፍና ላመጧቸው ለውጦች ምስጋና ለማቅረብ በመስቀል አደባባይ በወጣው እጅግ በርካታ ሕዝብ መካከል በአካል ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ለውጥ ጥቂት ተዋናይና ብዙ ተመልካች አይፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ተመልካቾች ውጤት ሲኖር ማጨብጨብና ሲጠፋ መውቀስ  ሳይሆን ወደ መድረክ ገብቶ መጫወት ያስፈልጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ ገናና የነበረች አገር ናት፤ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ፤ የድህነት ክንብንቧን አውልቃ የስንፍና ክንዶች ተላቃ ሌት ተቀን መትጋት እንደሚገባ አብራርተዋል። "አላማችን ሩቅ ነው፤ ግባችንም ሰፊ ነው" ያሉት ዶክተር አብይ፣ "ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንደምትመለስ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይኑራችሁ" ብለዋል። ለመሻገሪያ አቅጣጫዎች ግን ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ይገባል ነው ያሉት። “ምስጋናችን ከልብ የሚሆነው ልጆቻችንን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ስናሳድግ፣ ሴቶችን በእኩልነት ስንቀበል፣ ሌብነትና ሙስና ስንጸየፍ፣ ለአካባቢ ወገኖቻችን ስንቆረቆር በተግባር ስንተጋ ነው'' በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የእምነት አባቶች ሙስናና ዘረኝነትን እንዲያጠፉ፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ትናንትን በመርሳት በይቅርታና በፍቅር እንዲተጉ፣ ወጣቶች ለስራና ዕድገት እንዲሰለፉ፣ መምህራን ተማሪዎቻችሁን በዕውቀት እንዲመራ፣ ተማሪዎች በትጋትና በተስፋ እንዲራመዱ ጠይቀዋል። “አገራችንን ከወደድን ስልጣን እንደ ገዥነት ሳይሆን እንደ ኃላፊነት፣ መብታችን በመጠየቅ፣ ሹመትን በማገልገያነት፣ ሌብነትን እንጠየፍ፣ የሚፈናቀልን ሰው በወገናዊነት እንጠብቅ፣ የምትባክነውን ጊዜና ንብረት በመቆርቆር ለአገራችን ዘብ መቆም ይገባናል'' ሲሉ ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም