የፌዴራል ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የአሰራር ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ

116
ኢዜአ ታህሳስ 10/2012…የፌዴራል ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና ለማዘመን የሚያስችል የአሰራር ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ። የዚህ አካል የሆነውና ኮሚሽኑ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ረቂቅ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል መመስረቻና ትግበራ መመሪያዎችን ለማዳበር ግብዓት ለማሰባሰብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል። የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ በውይይቱ ወቅት በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመንግስት አገልግሎት ሰጪተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸው ደረጃውን ያልጠበቀና የተገልጋዩን ፍላጎት ያላማከለ ነው። በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጡ የተገልጋዩን ቅሬታ የማይፈታ፣ የግልፅነትና የፍትሃዊነት ጉድለት የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰዋል። "ዩኒቨርስቲዎች ካለባቸው ችግሮች ውሰጥ ከመፈጸምና ከማስፈጸምጋር ይያያዛል "ያሉት ኮሚሽነሩ በተለይ የያዙት የሰው ሃይል ብቃት በሚጠበቀው ደረጃ የተገነባ አለመሆኑን ተናግረዋል። የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማዘመን፣ለማሻሻልና የሚጠበቅባቸውን ሚና በውጤታማነት እንዲጫወቱ የሚያግዝ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ መመሪያው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ ዜጎችም በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና ጥራቱን የማሻሻል ተግባራት ላይ በንቃት መሳተፍና የውጤቶቹም ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህና በተቋማዊ የአሰራር ማዕቀፍ እንዲታገዝ ለማስቻል ጭምር ታስቦ ሰነዱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ሰነዱ ቋሚ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል አደረጃጀት በመፍጠር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና የተጠያቂነት ስርዓት ለመዘርጋትም ወሳኝ እንደሆነ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል። በኮሚሽኑ የመንግሰት አገልግሎት ጥራት ዝግጅት ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ገመቺሳ ኢትቻ በበኩላቸው የፌዴራል ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል ማቋቋሚያና ትግበራ መመሪያ ሀገራዊ ለውጡ ያስተናገዳቸው የህዝብ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል። አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በተገልጋዩ፣ በተቋማቱ፣ በባለድርሻና አጋር አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስችልም አስረድተዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የለውጥና መልካም አስተዳደር ቢሮ የቅሬታ ባለሙያ አቶ ዴተሞ ከማል በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲዎች በቅሬታ አሰጣጥ ዙሪያ ወጥ የሆነ መመሪያ ባለመኖሩ በተገቢው እንዳይሰሩ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። "አሁን መመሪያው መዘጋጀቱ ተገልጋዮችን በአግባቡ ተቀብለን የምናስተናግድበትና ከኛ በላይ የሚሆን ጉዳይ ደግሞ ለሚመለከታቸው አካላት ለማደራጀት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" ብለዋል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ለውጥና ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ተክላይ በበኩላቸው ወጥ የሆነ ካውንስል መዘጋጀቱ ለመናበብን ለተጠያቂነት አመቺ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መልክ ለተማሪዎች የሚሰጧቸው አገልግሎት ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን መመሪያው ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም