በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ባለው የቦክስ ውድድር አራት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄደዋል

59

ኢዜአ ታህሳስ 10/2012 በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ባለው የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ አራት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ከትናንት በስቲያ በሆሳዕና ከተማ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ አራት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

በ81 ኪሎ ግራም ወንዶች ፍጻሜ የአዲስ አበባ ፖሊሱ ሰይፈ ከበደ የፌዴራል ፖሊሱን ተወዳዳሪ ገዛኸኝ ሮባን በሁለተኛ ዙር በበቃኝ አሸንፎታል።

በ91 ኪሎ ግራም ወንዶች ፍጻሜ የፌዴራል ፖሊስ ሙሉቀን መልኬ የድሬዳዋ ከተማውን ተወዳዳሪ ግርማ አበበን በአንደኛ ዙር በበቃኝ ማሸነፍ ችሏል።

በ51 ኪሎ ግራም ሴቶች ፍጻሜ የጎንደር ከተማዋ አገሬ እማኙ የአዲስ አበባ ፖሊሷን ተወዳዳሪ ሮማን አሰፋ በነጥብ አሸንፋለች።

በ60 ኪሎ ግራም ሴቶች የአዲስ አበባ ፖሊሷ ቤተል ወልዱ የሀድያ ዞን የቦክስ ቡድን ተዳሪዋን ልዕልት ታረቀኝን በአንደኛ ዙር በበቃኝ ማሸነፍ ችላለች።

ነገ በውድድሩ የፍጻሜ ቀን ስድስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በ52፣ 57፣ 63፣ 69 እና 75 ኪሎ ግራም ወንዶች እና በ57 ኪሎ ግራም ሴቶች የሚካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮች መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጎንደር ከተማ፣ ሀድያ ዞን፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የሶማሌ ከተማ የቦክስ ክለቦች የውድድሩ ተሳታፊ ናቸው።

በወንዶች ከ52 እስከ ከ91 ኪሎ ግራም በላይ፤ በሴቶች ከ51 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

የውድድሩ አላማ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር በቦክስ ስፖርት ለመሳተፍ የካቲት 2012 ዓ.ም በሴኔጋል ለሚካሄደው የማጣሪያ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ ነው።

ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት ውስጥ አራት ጊዜ ይካሄዳል።

በዓመቱ ውስጥ የሚካሄዱ ቀሪ ሶስት ውድድሮች በጎንደር፣ በወላይታ ሶዶና በአዲስ አበባ ከተሞች እንደሚካሄዱ የቦክስ ፌዴሬሽኑ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም