የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ያስፈልጋል

116
ኢዜአ ታህሳስ 10 / 2012 -- የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በጋምቤላ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 24ኛው አገር አቀፍ ዓመታዊ የጊኒ ዎርም በሽታ የማጥፋያ መረሃ ግብር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳሬክተር ዶክትር በየነ ሞገስ በግምገማው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት የጊኒ ዎርም ሽታን ለማጥፋት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረትና ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። በሽታው ቀደም ሲል በሰው ላይ ብቻ ሲከሰት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሰው አልፎ በቤትና በዱር እንስሳት ላይ በተለይም በውሻ፣ በድመት፣ በዝንጀሮና ሌሎች ላይ መከሰቱን አመልክተዋል። ይህም በሽታውን ከክልሉ ብሎም ከአገሪቱ ለማጥፋት እየተካሄደ ያለውን ጥረት ውስብስብ እያደረገው መምጣቱን ገልጸዋል። በመሆኑም በሽታውን ለመከላከልና ለማጥፋት በሚከናወነው ሥራ ከህብረተሰቡ ጀምሮ የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይም የግብርና፣ የውሃ፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎች ተቋማት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስልግ ምክትል ዳሬክታሩ ተናግረዋል። በካርተር ሴንተር የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ዘሪሁን ታደሰ በበኩላቸው "እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ የሰው በሽታ ሆኖ ይታወቅ የነበረው የጊኒ ዎርም በሸታ በአሁኑ ወቅት የቤትና የዱር እንስሳትን ጭምር እያጠቃ ነው። ስለሆነም ሰዎች እንዲሁም የዱርና የቤት እስንስሳት የሚጋሯችው የውሃ አካላት ላይ የበሽታው ስርጭት ሊስፋፋ እንደሚችል ጠቁመዋል። በመሆኑም በሽታውን ለማጥፋት በሚከናወኑ ሥራዎች በእንሳስት ጤና እንክብካቤ የሚሰሩ አካላትም በመረሃ ግብር ተካተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። በሽታው ባለፈውና እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት በሰው ላይ አለመከሰቱን ጠቁመው ይህም በዘርፉ የተሻሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው አመላካች መሆኑን ገልጸዋል። "ካርተር ሴንተር በአገሪቱ በሽታውን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ድጋፉን አጠናከሮ ይቀጥላል" ብለዋል ዶክተር ዘሪሁን። ከሦስት ዓመት በፊት በሽታው በክልሉ በወርርሽኝ መልክ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ ናቸው። ይሁን እንጂ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በተሰሩ የተጠናከረ ቅንኝት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ስራዎች በሽታውን በሰው ላይ እንዳይከሰት ለመግታት መቻሉን አስረድተዋል። በቀጣይ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እንዳሚሰራም አስታውቀዋል። በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማው ላይ የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዩች ተሳታፊዎች ነበሩ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም