በሙስና ወንጀል የተመዘበረ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ለመንግስት ገቢ ማድረጉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ

95

ኢዜአ ታህሳስ 10/2012 ባለፉት አምስት ወራት በተደረገ ምርመራ በሙስና ወንጀል የተመዘበረ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግስት ካዝና በጥሬ ገንዘብ መመለሱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ እና የህግ የበላይነት፣ የሙስናና የፍትህ ማሻሻያን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚሁ ወቅት የጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ በሙስና ከተለያዩ የፌዴራል መንግስት ተቋማት የተመዘበረ ገንዘብ በተደረገ ምርመራ በማስረጃ በመረጋገጡ ክስ ተመስርቶ በተለያዩ አማራጮች ለመንግስት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ተግባር ባለፉት አምስት ወራት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግስት ካዝና በጥሬ ገንዘብ ተመልሷል ብለዋል።

ከ2009/2010 በኦዲት ግኝት በፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ያለ አግባብ ለብክነትና ለሙስና የተጋለጡ ሳይወራረዱ የቀሩ 312 ሚሊዮን ብር ሂሳቦች እንዲወራረዱ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል።

በቀጣይም በመንግስት ልማት ድርጅቶች፣ በፌዴራል ተቋማት፣ በግብይት፣ በሽያጭ፣ በብድር ተመላሽ ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስመለስ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ እየተሰራ ይገኛል ሲሉም ጠቁመዋል።

ከአገር የሸሹ ሀብቶችን ለማስመለስ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንና ሀብት የሸሸባቸውን አገራት በመለየት ከአገራቱ ጋር ውይይት መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይ የገንዘቡ መጠንና አገራቱ ለህዝብ ግልጽ እንደሚሆኑ አቶ ዝናቡ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ከሚፈጸምባቸው አገሮች ተርታ የምትመደብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ''መንግስት ይህን ለማስቀረት በትኩረት እየሰራ ይገኛል'' ብለዋል።

በተያያዘም ከመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እና በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበሩት ግጭቶች የተጠረጠሩ 266 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል።

በዚህም በኦሮሚያ ክልል በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለው ከተጠረጠሩ 337 ሰዎች ውስጥ 250ዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ደግሞ ከ16 በላይ ተጠርጣሪዎች ተለይተው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን አገሪቱ ባለችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ ለአገር ሰላምና ደህንነት ችግር ከሆኑት መካከል የጥላቻ ንግግርና አደገኛ መረጃዎች ስርጭትና ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ አዳዲስ ህጎች ለመጽደቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም