አገርንና ህዝብ በማስቀደም ለመስራት የሚያስችል ግንዛቤ ጨብጠናል - ጋዜጠኞች

54
ኢዜአ ታህሳስ 10/2012.. ስልጠናው የመገናኛ ብዙሃን የአገር ሰላምና ልማትን የጋራ አጀንዳ አድርገን እንድንሰራ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ በዘርፉ ለአንድ ወር ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ ከተለያየ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከቻይና መንግስት የኮሙኒኬሽን ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ለ76 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአንድ ወር ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናው በዋናነት በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ነባራዊ ሁኔታና መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን በተለይ በሰላምና መፍትሄ አምጪ ጋዜጠኝነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ከህዝብና ከግል መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡትን የጋዜጠኞች ቡድን ስልጠና ለመስጠት ባጠቃላይ 10 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን ብሮድካስት 4 ሚሊዮን እና የቻይና ኮሙኒኬሽን ዩኒቨርስቲ 6 ሚሊዮን ብር ሸፍነዋል። የስልጠናው ተካፋዮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ስልጠናው ወቅታዊና በኢትዮጵያ ሰላምና ልማትን ለማምጣት ዘርፉ የራሱን ሚና እንዲጫዎት የሚያደረግ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙሃኑ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ መስመር የለም ያሉት ጋዜጠኞቹ፤ በቀጣይ የአገር ሰላምና ልማት የጋራ መስመር እንዲሆን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ለዚህም ከሁሉም የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጣ ማህበር መቋቋሙንና ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የአቅም ግንባታ እስከመስጠት ለመድረስ መስማማታቸውንም ተናግረዋል። በቻይና ኮሙኒኬሽን ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ኮሙኒኬሽን ሴንተር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዥንግ ያንኩይ በበኩላቸው ''ስልጠናው በዚህ ወቅት መሰጠቱ መገናኛ ብዙሃኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛ የመረጃ ተደራሽ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል'' ብለዋል። በሃሳብ ተራርቀው ግጭትን የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎችንም ወደራሳቸው ተመልሰው ለአገርና ለህዝብ ጥቅም እንዲሰሩ የራሱ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው ስልጠናው የግልና የህዝብ፣ እንዲሁም በተለያየ አመለካከት ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እንዴት በአንድ ላይ መስራት እንዳለባቸው የተስማሙበት መድረክ እንደነበር ገልጸዋል። ይህ ስልጠና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥልና በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት  ከቻይና መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የአቅም ማነስ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም