የሳተላይቷ መምጠቅ በህዋ ሳይንስ መስክ አገራችንን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አነሳስቶናል---የስቲም ማዕከል ሰልጣኞች

114
ሀኢዜአ ታህሳስ 10 / 2012--ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ በትምህርታቸው ውጤታማ በመሆን አገራቸውን በመስኩ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ተናገሩ። በሃዋሳ ከተማ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው በዩኒቨርሲቲው ስቲም ማዕከል በሳይንስ ዘርፍ እየሰለጠኑ ያሉ ተማሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፣ ዛሬ የመጀመሪያዋ ሳተላይት መምጠቋ በቀጣይ በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው በዘርፉ አገራቸውን ይበልጥ ለማገልግል መነሳሳት ፈጥሮባቸዋል። የዩኒቨርሲቲው ስቲም ማዕከል ሰልጣኝና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ተማሪ አቢጊያ መስቀሉ እንዳለችው ሳተላይቷ በስኬት በመምጠቋ በእጅጉ መደሰቷን ተናግራለች። ሳተላይቷ ስትመጥቅ በቴሌቪዝን መስኮት ማየቷ በቀጣይ በጠፈር ምርምር ለመሰማራት መነሳሳት እንደፈጠረባት የገለጸችው ተማሪዋ፣ ይህንንም ለማሳካት ከወዲሁ በርትታ እንደምትማር ተናግራለች። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮያ የሚስተዋሉ ተስፋ ሰጪ አጋጣሚዎችን ወጣቱ ትውልድ በአግባቡ ሊጠቀምበትና ሊተጋ እንደሚገባ ጠቁማለች። “ዛሬ አንድ ተብሎ የተጀመረው ሳተላይት የማምጠቅ ሥራ ወደፊትም አጠናክሮ በማስቀጠል አገርን በተለያየ መስክ ማልማት ይገባል” ብላለች። በሳተላይቷ መምጠቅ ደስታውን የገለጸው ሌላው የማዕከሉ ሰልጣኝና የ12ኛ ክፈል ተማሪ የሆነው አረጋ አየለ ነው። እንደተማሪው ገለጻ የሳተላይቷ መምጠቅ እርሱን ጨምሮ በበርካታ ተማሪዎች ላይ መነሳሳትን ከመፍጠር ባለፈ ወደፊት በመስኩ የሚሰማሩ በርካታ ተማሪዎች እንዲኖሩ ያደርጋል። “ሳተላይቷ ስትመጥቅ የቀጥታ ስርጭቱን የተከታተሉ ኢትዮጵያዊያን የሚሰማቸው የተለየ ስሜት ይኖራልና፣ እኔም ራሴን እንደገና እንድፈትሽ አድርጎኛል” ሲል ገልጿል። በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ መምህሩ ዶክተር ምስራቅ ጌታሁን እንዳሉት በአገራችን በህዋ ሳይንስ ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም በቴክኖሎጂ ከመደገፍ አንጻር ክፍተቶች አሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስኩ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ምስራቅ፣ “አገራችን በምህዋር ውስጥ የምትሽከረከር ሳተላይት ባለቤት መሆኗ እጅግ የሚያስደስት ነው።” ብለዋል። እንደ ዶክተር ምስራቅ ገፈለጻ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሳተላይት ማምጠቋ ወደፊት በመስኩ ብዙ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ከመሆኑ በላይ በወጣቱ ዘንድ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም