ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ወጣቶች ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ የሚያደርግ ዕድል ነው

68
ኢዜአ ታህሰስ 10/2012.. የኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ ወጣቶች ወደ ዘርፉ እንዲሳቡና የአገራቸውን ብልጽግና ለማረጋገጥ እንዲተጉ መንገድ ከፋች ዕድል ነው ተባለ። ኢትዮጵያ ዛሬ ማለዳ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳተላይት ከቻይና ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ህዋ ልካለች። ማለዳ ላይ እንጦጦ በሚገኘው የሳተላይቷ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ወደ ህዋ ስትወነጨፍ ለመከታተል በዚያ የተገኙ ተሳታፊዎችም ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯን የሚያመላክት ነው ብለዋል። የስፔስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ በተለይም እንደ ኋላቀር ታዳጊ አገር ከቀዳሚዎቹ አገራት ጋር እኩል እንድትሄድ የሚያስችል ዘርፍ በመሆኑ የፕሮጀክቱ እውን መሆን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋል። ወጣቶች ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ቅርብ እንደመሆናቸው የአገሪቷ ሳተላይት ማምጠቅ ወደ ዘርፉ እንዲሳቡና የአገራቸውን ብልጽግና እንዲያረጋግጡ የሚያስችል ዕድል እንደሆነም ተናግረዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃቸው ከኢትዮጵያ ያነሰ አገራት በስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ተጠቃሚ በመሆን ዛሬ ጥሩ የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል። በስልጣኔ ቀደምት የነበረች አገር ዛሬ ወደኋላ ብትቀርም ቀደምት ስልጣኔዋን የሚመልስ ተስፋ ሰጪ ተግባር ነው፤ ያም ሆኖ 'ብዙ ቀሪ ስራዎች አሉ' ይላሉ ፕሮፌሰሩ። አሁን ካለው ተስፋ ጀርባ ከባድ ስራ የሚጠበቅ በመሆኑም ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማስተማር ሳተላይት መስራትና ማምጠቅ የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚገባ ይናገራሉ። የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው ደግሞ 'የማይቻል የሚመስለውን ነገር በተግባር ችለን ያሳየንበት ሁነት ነው' ሲሉ ገልጸውታል። የኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ 1ኛ ሳይንስ አካዳሚ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎቹ ብሩክታዊት መርሻ እና ኤልያስ ወልዱ ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። ለአገራቸው በምን ዘርፍ ምን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ እንዲያስቡ መነሳሳት የፈጠረ ተግባር መሆኑን ነው የሚናገሩት። ሳተላይቷ በቻይና እገዛ ከዚያው ትምጠቅ እንጂ ተቆጣጣሪዋም፣ አዛዧም ኢትዮጵያ ነች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም