ሳተላይት ማምጠቅ ሲባል የማይጨበጥ ነገር ይመስለን ነበር - አስተያየት ሰጭዎች

85
ኢዜአ፤ታህሳስ 10/2012 የኢትዮጵያ ስለሆነችው የመጀመሪያዋ ሳተላይት መምጠቅ አስተያየታቸውን ከሰጡ መካከል አንዱ 'ሳተላይት ማምጠቅ ሲባል የማይጨበጥ ነገር ይመስለኝ ነበር፤ ኢትዮጵያ ለዚህ ደረጃ በመብቃቷ ደስ ብሎኛል' ይላል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ "አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር እንደሚቻል በተግባር አሳይተናል" ብሏል። ኢትዮጵያ ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር ከቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኝ ማስወንጨፊያ ኢ.ቲ.አር.ኤስ.ኤስ-1 ማይክሮ ሳተላይት ዛሬ አምጥቃለች። ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የሚቆጣጠሯት ማይክሮ ሳተላይት በየ30 ደቂቃው የግብርና፣ የማዕድን፣ የአየር ትንበያና ሌሎች መረጃዎችን ታቀብላለች ተብሏል። በታሪካዊው ቀን ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች አዲስ አበባ የተገኙ እንዲሁም የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ስለ ሳተላይቷ ስሜታቸውን ለኢዜአ አጋርተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ሳተላይት ማምጠቅ ሲባል እውነት አይመስለንም ነበር፣ አሁን ግን ኢትዮጵያ በማምጠቅ በተግባር አሳየችን፣ በአገራችን ኮራን በማለት ነው አስተያየታቸውን የሰጡት። ወጣቶች የተከፈተውን በር በመጠቀም ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ የዳበረች አገር እንደሚያደርጓትም እምነታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የተለያዩ መረጃዎችን መሰብሰብ ያስችላታልም ብለዋል። ከኢትዮጵያ በቀጣይ ብሩህ ጊዜ እንጠብቃለን ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በአንድነት፣ በቅንጅትና በትብብር መስራት ከእኛም ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ዛሬ የመጠቀችው ሳተላይት መስራት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ነው ይላሉ። የራሳችንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን በራሳችን አቅም ሰርተን ማምጠቅ የምንችልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል። ሌሎች አገራት ሳተላይት ሲያመጥቁ በሙከራ ደረጃ ነው እኛ ግን ቀጥታ ወደ ተግባር ነው የገባነው ያሉት ደግሞ የሚኒስቴሩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነው ናቸው። ወደ ህዋ የመጠቀችው ማይክሮ ሳተላይት እንጦጦ ከሚገኘው ማዕከል በየ30 ደቂቃው መረጃ ማቀበል መጀመሯን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ሳተላይት የማምጠቅ ዕቅድ እንዳላትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም