ሳተላይቷ የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሰረት ነች... ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

92

ኢዜአ፤ ታህሰስ 10/2012.. የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የአገሪቷ የብልጽግና ጉዞ መሰረት መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

'ETRSS-1' የተሰኘችው የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ዛሬ ማለዳ ወደ ህዋ ተወንጭፋለች።

'ETRSS-1' ቻይና ከሚገኝ ማምጠቂያ ማዕከል ነው በማለዳው ወደ ህዋ የመጠቀችው።

በአዲስ አበባም ይህን ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ለማብሰር እንጦጦ በሚገኘው መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሳተላይቷ ወደ ህዋ ስትወነጨፍ የመከታተል ስነ-ሥርዓት ተከናውኗል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና  የፌዴራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ታድመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክትም ዛሬ ወደ ህዋ የተጓዘችው የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የአገሪቷ የብልጽግና ጉዞ መሰረት መሆኗን ገልፀዋል።

'ኢትዮጵያ ዛሬ እጅግ አኩሪ ተግባር ፈጽማለች' ያሉት አቶ ደመቀ ይህ የቴክኖሎጂ ልማት ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን በጠበቀ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከየብስ ተሻግሮ በህዋ ሳይንስ ሊኖር የሚገባውን የተወዳዳሪነት አቅም ከወዲሁ መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አገሪቷ በስፔስ ሳይንስ ልማት ጉዞ ለደረሰችበት የዕድገት ምዕራፍ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ግለሰቦች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተቋማትና አጋር አካላትም ምስጋና ቸረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው ሳተላይቷ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በኢትዮጵያዊያን ስለ ኢትዮጵያ መረጃ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ሳተላይቷ ከግምት ወደ እርግጠኝነት፣ ከተውሶ መረጃ ወደ ራስ ባለቤትነት የተረጋገጠባትና አገሪቷ ከድህነት በመውጣት ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ አስተዋፅኦዋ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከሳተላይቷ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር የኮሙኒኬሽን ሳተላይትና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ማዕከል ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂአን በበኩላቸው 'ቻይና ከ50 ዓመታት በፊት የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ ስታመጥቅ ደሃ አገር ነበረች' ነው ያሉት።

አሁን ግን ቻይና የቴክኖሎጂ ልማቷን ሌት ተቀን በማሳደግ ዓለም ላይ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት ተርታ የምትሰለፍ ታዳጊ አገር መሆኗን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያም ያሏትን መልካም ዕድሎች በቴክኖሎጂ በመጠቀም የብልጽግና ጉዞዋን ማሳጠር እንደምትችል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ህዋ መመንጠቅ የሁለቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት ፍሬ በመሆኑ የበለጠ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በስኬት የመጠቀችውን ሳተላይት ለግብርና፣ ለደንና አየር ንብረት ጥበቃ፣ ለማዕድንና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ጥናት፣ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና መረጃ ለመሰብሰብ እንደምትገለገልባት ታውቋል።

የሳተላይቷ ግንባታ ከቻይና ጋር በመተባበር የተከናወነ ሲሆን 20 ኢትዮጵያዊያን ኢንጂነሮች ተሳትፈውበታል።

ሳተላይቷን የመቆጣጠርና መረጃዎች የመሰብሰብ ስራውም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን መሃንዲሶች ይከናወናል።

ኢትዮጵያ ወደፊት በኮሙኒኬሽንና ብሮድካስት ሳተላይት ለማምጠቅና በምስራቅ አፍሪካ ከሳተላይት አገልግሎት የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትን ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ በ1950 ዎቹ የህዋ ሳይንስ ሀሳቡ የነበራት ቢሆንም እንደ ዛሬው ከ70ዎቹ አገራት አንዷ የሚያደርጋትን ስኬታማ ተግባር ለመከወን ሳይቻል መቅረቱንም መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም