ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጠቀቻት ሳተላይት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ታደርገናለች... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

286

ታህሳስ  10/2012 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጠቀቻት ሳተላይት ግብርናን ለማዘመን፣ በእውቀትና በመረጃ ላይ የተሰመረተ ስራ ለመስራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድንሆን ታደርገናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ላመጠቀቻት ሳተላይት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዛሬ ማለዳ ETRSS-1 የተሰኘችው የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወደ ህዋ መጥቃለች።

ይህ 'በታሪካችን የመጀመሪያ የሆነው ሳተላይት የመጨረሻ ሳይሆን የመጀመሪያችን ነው' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።

ወደ ህዋ የመጠቀችው ሳተላይት በዋናነት ግብርናን ለማዘመን፣ በእውቀትና በመረጃ ላይ ተንተርሰን ስራችንን እንድንሰራም የምታደርግ ናት ብለዋል።

እንዲሁም በአፍሪካና በመላው ዓለም ገበያ በእውቀት ላይ ተመስርተን ተወዳዳሪና ውጤታማ እንድንሆን የምታግዝ እንደሆነችም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የራሷ ሳተላይት ስላልነበራት መረጃዎችና ምስሎችን ከተለያዩ አገራት በግዢ ታገኝ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ሳተላይቷ የድንበር አካባቢ እንቅስቃሴዎችና ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የምንከታተልባት ትሆናለች ብለዋል።

የአገሪቷን የአየር ጠባይ ለመከታተል እንዲሁም በቂ መረጃ በመሰብሰብ ለውድድር እንድንበቃ መሰረት ሆና ታገለግላለችም ብለዋል ዶክተር አብይ።

በዚህ የሳተላይት ማምጠቅ ሂደት ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ሙያተኞች ከዲዛይን እስከ ምርት ድረስ የተሳተፉ ሲሆን የቁጥጥር ማዕከሉ ሙሉ ለሙሉ አዲስ አበባ ላይ መሰራቱም አበረታች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ወደ ምህዋር የጀመረችውን እንቅስቃሴ፤ የመረጃና የእውቀት ፍለጋ ጅማሮ በፍጥነት በማስቀጠል ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ መጀመሩንና ለትውልድም የሚተላለፍ መሆኑን አክለዋል።

አብዛኛው የሳተላይቷ ወጪ በቻይና መንግስት የተሸፈነ ሲሆን ወደፊት ከተለያዩ አገራት ጋር በመሆን አዳዲስ ሳተላይቶችን ለማምረት ጥረት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሳተላይቷ ቻይና ከሚገኝ ማምጠቂያ ማዕከል ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ማለዳ ወደ ህዋ መጥቃለች።

72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው የቻይና ስሪት ሳተላይት ምልከታዋ በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ አካባቢዎች ሆኖ በሰሜንና ደቡብ በ80 ዲግሪ ላቲቲውድ ላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በጠፈር ሳይንስ ዘርፍ በዓለም ላይ አሜሪካ 450 የሚሆኑ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ያሏት ሲሆን ቻይና ደግሞ 245 የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች እንዳሏት መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም