ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ወደ ቀድሞ የስለጣኔ ማማዋ መመለሷን ያመላከተ ነው...የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

81

ኢዜአ፤ ታህሳስ 10/2012 "ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ መብቃቷ ጥንት ወደ ነበረበችበት የስልጣኔ ማማ ለመመለስ ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው "ሲሉ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።

የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የዘርፉ ተማሪዎች በቻይና የተካሄደውን የ“ኢት አር ኤስ ኤስ አንድ” ሳተላይት  የማምጠቅ ስነ-ስርዓትን በተቋሙ ጥበብ ህንጻ አዳራሽ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ተከታትለዋል ።

ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ፍሬው ተገኘ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አባቶች ከነጻነት ተጋድሎ ባሻገር በህዋና በስነ ምድር ጥናት የቀደምት ታሪክ ባለቤት ነበሩ።

በጊዜ ሂደት በተፈጠሩ ውስጣዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ምክንያት የነበሩ የህዋ ሳይንስ፣ የስነ ምድርና ሌሎች የቴክኖሎጂ እውቀቶች እየጠፉ መምጣታቸውን አውስተዋል።

"አሁን ላይ የእውቀት ምንጭና መሰረት ለሆነው ዘመናዊ ትምህርት ትኩረት በመሰጠቱ ሀገራችን የራሷን ሳተላይት በማምጠቅና በህዋ ላይ የራሷን አሻራ በማሳረፍ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍታለች" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችና አመራሮችን በማፍራት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የህዋ ሳይንስ ምርምር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር የባህርዳር ሰብሳቢ፣ የስፔስ ፊዚክስ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጸጋዬ ካሳ በበኩላቸው የስፔስ ሳይንስ እውቀት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋና ተቀባይነት እንዲያገኝ ማህበሩ በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፔስ ፊዚክስ ፕሮግራምን በመቅረጽ እሰከ ሶስኛ ዲግሪ ደረጃ  ባለሙያ በማሰልጠንና በዘርፉ ምርምር በማካሄድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የዘርፉ ልማት እየደገፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዛሬ የመጠቀችው ሳተላይት በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት በመሆን በኢትዮጵያ ምድር ያሉ እንቅስቃሴዎችን የመሬት ምልከታ በማካሄድ መረጃን ወደ እንጦጦ ማዕከል የምትልክ መሆኗንም ጠቁመዋል።

የግብርና ምርትን ለማዘመን፣ የሚደርሱ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ቀድሞ ለመተንበይ፣ የማዕድን ሃብትን፣ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃን ለማልማት ሳተላይቷ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ መረጃን በመቀበልና በመላክ ሳተላይት ላላቸው ሀገራት በየዓመቱ የምትከፍለውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት ለለሀር ልማት ለማዋል ያላት ፋይዳም የጎላ ነው።

ማህበሩ በራሱ ባለሙያዎች ባሰለጠናቸው ከሳተላይቷ የሚመጣን መረጃ የመቀበል፣ የመተንተንና ወደ ጥቅም የመለወጥ ስራ የሚሰራ በመሆኑ በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት መሰረት መሆኑን ተመራማሪው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ጨምሮ 10 ያህል ሌሎች ሳተላይቶችን በማምጠቅ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የሚኖራትን ሚና ለማሳደግ እየሰራች መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም