አንዳችን ለአንዳችን የመኖር እንጂ የመጥፋት ምክንያት መሆን የለብንም---የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች

56
ኢዜአ ታህሳስ 8 ቀን 2012 ወጣቶች አንዳችን ለሌላችን የመኖር እንጂ የመጥፋት ምክንያት መሆን የለብንም ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ገለጹ፡፡ “ ፒስ ሞዴልና ቲክቫይ ኢትዮጵያ “ የተባለ የግል ማህበር "ሰው መሆን" በሚል ርዕስ ከአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ጋር በሰላም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡ መቀመጫውን ሃዋሳ ከተማ ያደረገው ማህበሩ በሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ይቅርታ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው፡፡ የውይይት መድረኩ አስተባባሪ ወጣት ማህደር ዘነበ በውይይቱ ላይ ለወጣቶቹ ባስተላለፈው መልዕክት እንዳለው ወጣቶች አንዱ ለሌላው የመኖር እንጂ የመጥፋት ምክንያት መሆን የለባቸውም። "በአንዱ ማደግ ሌላው እንደሚያድግ፣ በውድቀትም የአንዱ ለሌላው እንደሚተርፍ ማመን ከተቻለ እርስ በርስ የመደጋገፍና የአብሮነት ባህላችን ይጎለብታል" ብሏል፡፡ "ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በአገራችን የሰውነት ክብር እየቀነሰ ዜጎች በተለያየ ስፍራ ለግጭትና ለጉዳት ሲዳረጉ ይስተዋላል" ያለው ወጣቱ፣ ይህም  በነገ ተስፋ ላይ ጽልመት የሚጋርድ በመሆኑ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባ መከሯል። "የሰውነት ክብር ከሁሉ ይልቃል" ያለው ወጣቱ " የተለያየ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት ቢኖረንም ቅድሚያ ሰው መሆናችን አንድ እንደሚያደርገን ሊዘነጋ አይገባም" ብሏል፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚኖረው ወጣት በፈጣሪ አሰፋ በበኩሉ "በአንድ አገር የምንኖር የሰው ዘር በመሆናችን አርስ በርስ ከመጎዳዳት ይልቅ ለሌሎች መኖር ምክንያት መሆን አለብን" ብሏል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ በመስራት ያሰቡትን ለማሳካት ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የገለጸው ወጣቱ "አንዱ ለሌላው የጥፋት ምንጭ ከሆነ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም" ብሏል። ሁሉም ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነትና ለይቅርታ ራሱን በማዘጋጀት ተባብሮ መስራት ከቻለ አገርና ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጿል፡፡ "የአገርን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ሁሉም አዎንታዊ ሚና ካልተጫወተ መጻኢ ዕድላችን አደጋ ላይ ይወድቃል" ያለችው ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት እጹብድንቅ አባተ ናት፡፡ "እኛ ወጣቶች የአባቶችን ምክር መስማት አለብን " ያለችው ወጣቷ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በጥሩ ስነ-ምግባር አንጸው የማሳደግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቃለች። ያለሰላም በአንድ አገር ተረጋግቶ መኖርና መስራት እንደማይቻል የገለጹት ደግሞ በመድረኩ ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባት ቄስ ያዕቆብ ጮሌ ናቸው፡፡ ከኑሮ በላይ ሰላም አሳሳቢ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው፣ የሰላም አለቃ ፈጣሪ በመሆኑ የእርሱን አርአያነት መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ "በተለይ የአባቶችን ምክርና ግሳጼ ሰምተው ከጥፋት ተግባር የተመለሱ ወጣቶች የጋሞ አባቶችን የሰላም ተምሳሌትነት በማስቀጠል ለዓለም ማስመስከር ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡ በጋሞ ዞን አንጻራዊ ሰላም እንዲኖር ለባህላቸው ታማኝ የሆኑ የጋሞ አባቶችና ወጣቶች በውይይት መድረኩ ላይ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም