በትግራይ ከ560 ሺህ በላይ ሰዎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

60
ኢዜአ ታህሳስ 8 /2012 ---በትግራይ ክልል በተያዘው ዓመት ከ560 ሺህ በላይ ሰዎችን የንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገለጸ። የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ፍቃዱ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ያለውን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለል 400 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው። በእዚህም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከ200 በላይ የሚሆኑ ጥልቅ፣ መካከለኛና አነስተኛ የውሃ ጉድጓዶች ግንባታ ሥራ ከዲዛይን እስከ ቁፋሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። "በማይጨው፣ ዓዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬ እንዳስላሴና ሽራሮ ከተሞች ያለውን የህዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚመጥን የውሃ አቅርቦት እንዲኖርም በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል አቶ ጌታቸው ። እንደእሳቸው ገለጻ የአዲግራትና የማይጨው ከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው በአሁኑ ወቅት ለአገልግሎት በቅተዋል። ለሽራሮ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲውል ቀደም ብሎ ለተገነባ አነስተኛ ግድብ የውሃ መተላለፊ መስመር ግንባታ ሥራ መጠናቀቁንና የኤሌክትሮ መካኒካል ገጠማ ሥራ እንደሚቀረውም አመልክተዋል። ለአክሱም ከተማ አገልግሎት የሚውል የግድብ ግንባታ ሥራ የዲዛይና ሌሎች የቅድመ ግንባታ ስራዎች መጠናቀቃቸውንም አቶ ጌታቸው አመልክተዋል። በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎችን ከማዳረስ በተጨማሪ ቀደም ብለው የተሰሩት የውሃ ተቋማት ዘለቄታዊነት እንዲኖራቸው ጥገና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ተቋማቱ ሲጠናቀቁ በአሁኑ ወቅት 57 በመቶ የሆነውን የክልሉ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 65 በመቶ እንደሚያሳድገው አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። የማይጨው ከተማ ውሃና ፍሳሽ ኃላፊ አቶ ኃይለ ተሰማ ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የከተማው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት ዘንድሮ እየተጠናቀቀ መሆኑን ነው የገለጹት። አቶ ኃይለ እንዳሉት ለከተማው አገልግሎት የሚውሉ የስምንት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የሦስት ውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታና የ14 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ ስራዎች ተከናውነዋል። ይህም በአሁኑ ወቅት 74 በመቶ ላይ የሚገኘውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 84 በመቶ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል። በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል '' ማይድሙ '' በተባለው ግድብ የሁለተኛ ምዕራፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሽረ እንዳስላሴ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አስተባባሪ አቶ ኃየሎም አርአያ ናቸው። እስካሁን የውሃ የማጣሪያና ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታ ሥራ መከናወኑን ገልጸው በከተማው የውስጥ ለውስጥ የውሃ መስመር ዝርጋታ ስራዎችም እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል። "ከዚህ ቀደም 40 በመቶ የነበረው የከተማው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ዘንድሮ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም