በሀገሪቱ ለሰላም እና ልማት ፓርቲዎች ተቻችለው በጋራ መስራት እንዳለባቸው የኦዴፒ አባላት ና ደጋፊዎች ተናገሩ

49
ኢዜአ ታህሳስ ዐ8/2ዐ12/ በሀገሪቱ ሰላም እና ልማት እውን እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባላት ተቻችለው በጋራ መሰራት እንዳለባቸው በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የኦዴፒ አባላት ና ደጋፊዎች ተናገሩ። በዞኑ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በብልፅግና ፓርቲ አላማ ፣ ኘሮግራምና ህገ ደንብ ዙሪያ እየተወያዩ ነው።በውይይቱ ወቅት አባላትና ደጋፊዎቹ እንዳሉት የፓርቲው አካሄድ በሀገሪቱ ተገቢነት ያለው ፌዴራሊዝም እንዲተገበር ብቻ ሳይሆን ዜጐች በህግ ለመዳኘት ትክክለኛ መስመር ነው። ከተሳታፊ አባላት መካከል አቶ ሙልጌታ ታዬ በሰጡት አስተያየት " የሀገር ልማትና እድገት እውን የሚሆነው ሁከትን በማስወገድ በመቻቻልና በመስማማት ለሰላም በጋራ በመስራት ነው" ብለዋል። በውህደት የመጣው የብልጽግና ፓርቲ ትክክለኛ ፌዴራሊዝምን በመተግበር ዜጎችን በእኩልነት ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል። ወይዘሮ ንግስት ኃይለመስቀል በበኩላቸው "አባላትም ሆኑ ደጋፊዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዓላማና ኘሮግራም በአግባቡ በመረዳት ለፓርቲያቸውም ሆነ ለህዝብ ድጋፍ መስጠት አለባቸው" ብለዋል። ይህም የህዝብ ጥያቄዎችና ችግሮች በየትኛው ኘሮግራም ይመለሳል የሚለውን ለመፍታት ግንዛቤው ወሳኝነት እንዳለው በማመን በውይይቱ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። የፓርቲው አባላት ለቆሙለት ዓላማና ኘሮግራም እውቅና ከመስጠት ባሻገር በመዋቅሩ ውስጥ በንቃት መንቀሳቀስ አስፈላጊ እንደሆነም የገለጸው ደግሞ ወጣት ስዩም ክብሩ ነው። ለብልፅግና ፓርቲ ኘሮግራምና ህገ ደንብ እውን መሆን በጐ አስተዋፅኦ ማበርከት ወቅቱ የሚጠይቀው እንደሆነም ጠቁመዋል ። የሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ፣ ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባላት መቻቻልን በማዳበር በጋራ ተባብረው መስራት እንዳለባቸውም አባላትና ደጋፊዎቹ ተናግረዋል። በዞኑ የኦዴፒ ሊቀመንበር አቶ እንዳሻው ብርሃኑ በበኩላቸው አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ በሀገር ውስጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል መሰረት መጣሉን ገልጸዋል። በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት በሚደረገው ትግል የአባላትና የደጋፊዎች አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል። እያንዳንዱ የፖለቲካ ኃይልም ሆነ ሌላው ዜጋ ለሀገሪቱ የተሻለ ለውጥና እድገት በትዕግስት ፣በመቻቻልና በህግ በመመራት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል። በሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከል እየተካሄደ ባለው ውይይት ከዞንና ከ13 ወረዳዎች  የተውጣጡ  አባላትና ደጋፊዎች እየተሳተፉ ነው    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም