በጉጂ ዞን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል እየተሰራ ነው

55
ኢዜአ ታህሳስ 8/2012  በጉጂ ዞን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ38 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነጻ የደም ምርመራ አገልግሎት መሰጠቱን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ ምርመራ ማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ አንዳንድ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የበሽታዎች ክትትል ባለሙያ ወይዘሪት ብርቷኪት ወርቅነህ የስኳር፣ የግፊት፣ የመህጸን ጫፍ ካንሰርና የደም መርጋት ምርመራ በሆስፒታል ደረጃ እየተሰጠ ነው፡፡ የነገሌ፣ የአዶላ፣ የቦሬና ኡራ ሆስፒታሎች ደግሞ ነጻ የደም ምርመራ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ከፍተኛ የጤና ተቋማት እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ በዞኑ በየአመቱ 215 ሺህ 264 ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሚጠቁ በጥናት መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡ የጤና ችግሮቹን ለመከላከል ካለፈው ሀምሌ ጀምሮ በጤና ተቋማቱ ነፃ የደም ምርመራ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው እስካሁንም 38 ሺ 128 ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ''ምርመራ አድርገው እራሳቸውን ካወቁ ውስጥ 749 ሰዎች የግፊት፣ 233 የስኳር፣ 65 ደግሞ የሌሎች ጤና ችግሮች የተጋለጡ መሆኑ ተረጋግጧል'' ብለዋል፡፡ በበሽታው ተይዘው ህመም ስለማይሰማቸው ጫት የሚቅሙ፣ መጠጥ የሚጠጡና የሚያማጨሱ በርካታ ሰዎች ለከፋ የጤና ችግር መዳረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡ የበሽታው ምልከት የታየባቸው ሰዎች በህክምና ክትትልና በስፖርት እንዲከላከሉ ምክር መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በዚህ አመት ለ250 ሺህ ሰዎች ነጻ የደም ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ወጣት ቴወድሮስ ነጋሽ የህመም ስሜት ባይኖረውም የደም መርጋት እንዳለበት ሰሞኑን በነገሌ ሆስፒታል ባደረገው ምርመራ እንዳወቀ ገልጿል፡፡ የምርመራ ውጤቱ ያላሰበውን በሽታ ያሳወቀው በመሆኑ ካሁን በኋላ በሽታውን ከሚያባብስ ጫትና መጠጥ በመቆጠብ በህክምና ክትትልና በስፖርት ለመከላከል መወሰኑን ገልጿል፡፡ ምርመራ በማድረግ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ነጻ የሆኑት ወይዘሮ አዳነች ገሰሰ የጤና ችግር እንዳይገጥማቸው በየጊዜው የህክምና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም