አዲሱ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል ጠየቀ

145
ኢዜአ ታህሳስ 8/2012 ባለፈው ሳምንት በምርጫ ቦርድ የምዘገባ ምስክር ወረቀት የተቀበለው 'ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ' የኢፌዴሪ ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል ጠየቀ። ፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ የመንግስት አወቃቀርና ለዘብተኛ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም እንደሚያራመድም አስታውቋል። የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደምና ሌሎች አመራሮች በፓርቲው ዓላማና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መገለጫ ሰጥተዋል። ፓርቲው በጠቅላላ ጉባኤ ከተመሰረተ ሰባት ወራትን ቢያስቆጥርም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ከተሰጠው አንድ ሳምንት መሆኑን ነው በመግለጫው የተጠቆመው። ፓርቲው ከነበረው የሴራና ጥሎ ማለፍ ፖለቲካ በጸዳ መንገድ አዲስ አስተሳሰብና የፖለቲካ ባሕል እውን እንዲሆን የሚሰራና የጠረፋማ አካባቢ ህዝቦችን ያካተተ የትግል ስልት እከተላለሁ ብሏል። ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷ እንዲከበርና ጠንካራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እንዲገነባ አበክሮ እንደሚሰራም ገልፆ፤ የብሔር፣ ቋንቋ፣ የኃይማኖትና ባህል ብዝሃነት እንዲከበርም ሚዛናዊ ፖሊሲ በመከተል ውስብስብ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ነው የገለጸው። የፖለቲካ ስልጣን ከህዝብ የሚመነጭበት ባህል እንዲሰርጽና በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ በሕግ የበላይነት፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሁም በባህልና አምልኮ ነጻነት ረገድ ትኩረት እንደሚሰጥም ገልጿል። እውቀት ተኮር ብሔራዊ የልማት ስትራቴጂን በመከተል በሰው ሃይል ልማት ላይ ያተኮረና በአገር ዕድገት ላይ ልዩ የፖሊሲ ሃሳብ ይዞ መምጣቱንም አስረድቷል። ፓርቲው የኢትዮጵያን ባህልና ዕድገት ተጨባጭ ሁኔታ ያማከለ ለዘብተኛ ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተልም ገልጿል። በመንግስት አወቃቀር ረገድም አሁን ካለው ፓርላሜንታዊ ስርዓት ይልቅ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓትን መርጧል። የመንግስት መዋቅር መለወጥ ያስፈለገውም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጽ የሚመረጥ ፕሬዝዳንት ተሰይሞ በህዝቦች መካከል ልዩነትን ለማጥበብና ጠንካራ መንግስት ለመመስረት ያግዛል በሚል አመክንዮ መሆኑንም ገልጿል። በሌላ በኩል የአሁኑ ፓርላሜንታዊ ስርዓት ጥምር መንግስት ለመመስረት አያስችልም የሚል አምነት እንዳለውም አብራርቷል። በሌላ በኩል ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለመመስረትም ሆነ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት እንዲታደስ ጠይቋል። ሕገ መንግስቱን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ እንዲቀየር የሚሹና ጭራሽ አይነኬ አድርገው የሚገልጹ ግራና ቀኝ ሁለት ጽንፍ የያዙ ወገኖች እንዳሉ ጠቁሞ፣ ፓርቲው ግን ሕገ መንግስቱ ጥናት ተደርጎበት መሻሻል እንዳለበት ነው ፍላጎቱን ያስታወቀው። መሻሻል የሚገባቸው ዝርዝር አንቀጾችንም ፓርቲው በራሱ ጥናት ማድረጉን ገልጾ፣ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቃል። ወቅታዊ ጉዳይን በተመለከተም በብዙ ትግል የመጣው ለውጥ በርካታ ትሩፋቶች በማምጣቱ እንደሚደግፈውና ጸረ ለውጥ ሃይሎችንም እንደሚቃወም አስታውቋል። በሌላ በኩል ላለፉት አንድ ዓመት ተኩል በተፈጠሩ ግጭቶች በርካቶቹ ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ጉዳት መድረሱና ግጭቱም መባባሱ የለውጥ አመራሩ ክፍተት መሆኑን ገልጿል ፓርቲው። ማንነትና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶችን እንደሚያወግዝም ገልጾ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቃዮችንም በዘላቂነት ለማቋቋም የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል። ምርጫን በተመለከተም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በደቡብና በሀረሪ ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መክፈቱን፣ ምርጫው ቢደረግም፣ ቢራዘምም ለምርጫ ጣቢያዎቹ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። ለአብነትም በምስራቅ አማራ 23 ወረዳዎች፣ በሞያሌ፣  ሀረሪ፣ በስልጤ ዞን ቅርንጫፍ መክፈቱንና በቅርቡም በጅግጅጋ፣ ጅማና ቦረና አካባቢዎች ጽህፈት ቤት እንደሚከፍት ገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም