ለኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ አገልግሎት የሚውለው ጨው በሚፈልገው መጠን እየቀረበ አይደለም ተባለ

101
ኢዜአ ታህሳስ 8/2012 ለተለያዩ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ምርቶች በጥሬ ዕቃነት የሚፈለገው ጨው በተገቢው መጠን እየቀረበ ባለመሆኑ ኢንዱስትሪዎች ለችግር እየተጋለጡ መሆኑ ተገለፀ። ጨውን ጨምሮ አስፈላጊ የኢንዱስትሪ ግብኣት የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ችግሩን ለመፍታት የሚጠበቅበትን ተግባር እንዲያከናውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል። ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው የድርጅቱን የአምስት ወራት የስራ አፈጻጸም ዛሬ በገመገመበት ወቅት ነው። ጨው በአገር ውሰጥ በከፍተኛ መጠን የሚገኝ ምርት መሆኑ ቢታወቅም ኢንዱስትሪዎች ግን በሚፈልጉት መጠን እየቀረበላቸው አይደለም ሲል ነው ቋሚ ኮሚቴው የገለፀው። ቋሚ ኮሚቴው በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው የመስክ ምልከታዎች ኢንዱስትሪዎች ከሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች መካከል አንዱ የጨው ጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት መሆኑን አንስቷል። በመሆኑም ከኢንዱስትሪ ጨው ምርትና አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲዘየድ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ አስገንዝበዋል። ድርጅቱ በአገሪቱ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትና ስርጭት ችግርን በመከላከል ሸቀጦችን በወቅቱ ለህብረተሰቡ ለማድረስ የሚያስችል ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋት ይጠበቅበታል ሲሉም አመልክተዋል። በተለይ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ታስበው የሚከናወኑ የሸቀጦች ግዢና አቅርቦትን በተመለከተ ልዩ ትኩረት በመስጠት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድርግ መስራት እንዳለበት አሳስቧል። ለተለያዩ ኢንዱትሪዎች በመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎቶች ላይ የሚውሉ ግብዓቶችን ለመግዛትና ለመሸጥ የተያዙ እቅዶች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ሊስተካከል እንደሚገባም አሳስቧል። ለቆዳ ፋብሪካ የሚውሉ የተለያዩ ኬሚካሎችና ቀለሞች ግዥና አቅርቦትም አነስተኛ መሆኑን ተጠቁሟል። ከዱቤ ሽያጭና አሰባሰብ ጋር በተያያዘም በውሉ መሰረት መሰብሰብ ላይም ሰፊ ችግር መኖሩን ቋሚ ኮሚቴው መገምገሙን ወይዘሮ የሺእመቤት ተናግረዋል። ድርጅቱ ለተለያዩ የኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውሉ ብረትን፣  ጨርቃጨርቅንና የበግ ሌጦን በተገቢው መጠን ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ረገድ ያከናወነው ተግባር በጥንካሬ ተነስቷል። የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት በቀጣይ የተሻለ ስራ ለማከናወን በድርጅቱ የተጀመረው ጥረትም አበረታች መሆኑም ተወስቷል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድአለው ሀብታሙ በበኩላቸው ከቋሚ ኮሚቴው የተነሱ አስተያየቶች አግባብ መሆናቸውን ገልጸው ችግሩን በቀጣይ ለመፍታት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ከጨው አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ከድርጅቱ አቅም በላይ በመሆኑ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት በኩል ችግሩ እንዲፈታ መጠየቁን ተናግረዋል። በዚህ ረገድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንዲያግዛቸው ሰብሳቢዋ ጠይቀዋል። በአፋር ክልል ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃነት የሚውለውን ጨው የማምረት ፍቃድ የተሰጠው ለአንድ ድርጅት ብቻ መሆኑ ለችግሩ መከሰት አንዱ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል። ዘይትን ጨምሮ መሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትን ለማሻሻል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም ገልፀዋል። በተለይም ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከውጭ አገር የተገዛው የምግብ ዘይት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደአገር ቤት እንዲገባ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማንሳት። በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ 71 ኮንቲኔር ዘይት ወደአገር ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም