ግብርና ና የግብርና ምርታማነት እድገት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ

253

በሰለሞን ተሰራ(ኢዜአ)

ግብርና የኢትዮጵያ ገበሬዎች የእለት ጉርስ ማግኛ፣ የገቢ ምንጭ፣ የአገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት፣ ከ70 በመቶ በላይ የአገሪቷን ህዝብ  ስራ ላይ ያሰማራ፣ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ እድገት ምጣኔ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማስገቢያም ነው።

ጊዜ ያለፈበት የአመራረት ዘዴ ምርታማነቱን በእጅጉ በማቀጨጭ "አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል" በማለት የዘ ጋርዲያን የደቡብ አፍሪካ ዘጋቢ በሐተታው ጠቅሶታል።

ኋላ ቀር የግብርና ዘዴው ገበሬውን ከእጅ ወደ አፍ ከሆነው ኑሮ ሊያላቅቀው ካለመቻሉም የበላይ ተመልካች አድርጎም ተቀምጧል።

የግብርናውን ዘርፍ ማሳደግ ከተቻለ ጤፍን የመሳሰሉ ተፈላጊ ሰብሎችን በበቂ ሁኔታ በማምረትና የአቅርቦት ዋስትናን በማረጋገጥ የውጭ ገበያን ታሳቢ ያደረገ አመርቂ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ይቻላልም ነው ያለው።

ኢትዮጵያ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና አበባን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ብትገኝም ከዘርፉ በሚገባት ልክ እየተጠቀመች አይደለም።

ነገር ግን አገሪቷ ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በመጠቀምና ምርታማነትን በማሻሻል የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ከሚገባው በላይ ማሳደግ እንደሚትችልም እምነት አለው።

ምንም እንኳን በታቀደው ልክ ባይሆንም መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ግብርናውን ወደ ሰፋፊ እርሻ በማሳደግ ለአገሪቷ የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳትና ቅድሚያ በመስጠት እየሰራበት ይገኛል።

በጥናት የተደገፈ ስኬታማ ሰፋፊ እርሻን መተግበር የግብርናን ምርታማነት ከመጨመር ባለፈ በርካታ የገጠር የስራ እድል ለመፍጠርም ያግዛል።

ዛሬ ላይ በአገሪቷ የሚታየው የግብርና አሰራር ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የአመራረት ዘዴ የተዋጠና በአነስተኛና በተበጣጠሰ ማሳ የሚታረስ ነው።

የግብርናው ምርታማነትና  የሚገኘው ሰብል ዝቅተኛ ሲሆን የዚህ ምክንያት ደግሞ ገበሬዎቹ በበቂ ሁኔታ ምርጥ ዘርና ፀረ ተባይ መድሃኒት የመሳሰሉ የግብርና ግብዓቶች አለማግኘታቸው ነው ብሏል።

በአነስተኛ ማሳ የሚያርሱ ገበሬዎች ዘመናዊ የተባለውን የግብርና ቴክኖሎጂ ካለመጠቀማቸው ባለፈ የአስተራረስ ዘዴያቸውና የመሬት አያያዛቸውም ደካማ ነው።.

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተደቀኑትን በርካታ ችግሮች በመጋፈጥ ግብርናዋን ለማዘመን እየታተረች ቢሆንም የለም መሬት እጥረት፣ የአየር ፀባይ ተለዋዋጭነት፣ የመሬት መራቆትና መሸርሸር፣ የእህል መዝሪያ ወቅት አጭር መሆን፣ ደካማ የትራንስፖርት ትስስር አቅርቦትና የብቁ ባለሙያ እጥረት ተግዳሮቶች አሉባት።

እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ደግሞ አገሪቷ የግብርና ዘርፉን ተደራሽ ማድረግ በፍጥነት የሚለወጥና በአርሶ አደሩ ዘንድ ቶሎ የሚለመድ ማድረግ አለባት።

ሰፋፊ እርሻዎችን ለማስፋፋት የሚወጣ ፖሊሲም ምርታማነትን በማሳደግ በሄክታር የሚገኘው ምርት እንዲጨምር እንደሚያግዝምና  ለመስኖ ልማት የሚውል ኢንቨስትመንት እና የመሰረተ ልማት መዋዕለ ንዋይም በረጅም የጊዜ ሂደት ዘርፉን ለማሳደግ ቁልፍ መዘወሪያ መሆኑን ዘገባው በሰፈው አትቷል።

ለአስቸኳይ መፍትሄ ደግሞ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና የተባይ ማጥፊያ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማበረታታት ይገባል ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ የአመራረትና የመሬት አያያዝ  ዘዴዎችን እንዲተዋወቁ ማድረግም ይጠቅማል።

ዘመኑ የደረሰበትን የአስተራረስ ዘዴ እውን ለማድረግ ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ ትላልቅ ኩባንያዎች ጥረቱን እውን ለማድረግ በአዳዲስ ቴክኖለጂ የታገዘ ድጋፍ መስጠታቸው የማይተካ ሚና እንዳለው ተጠቅሷል። ድጋፉ ምርጥ ዘርን፣ የሰብል አጠበበቅንና ዲጂታል የግብርና ቴክኖለጂ አቅርቦትን ያጠቃልላል።

ለምሳሌ ዘላቂነት ያለው ፀረ አረም እና የተባይ ማጥፊያ መጠቀም አርሶ አደሮቹ ምርታቸውንና የደረሰ ሰብላቸውን በቅድሚያ ለመከላከል ያስችላቸዋል ብሏል።

በዓለም እየጨመረ የመጣውን የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላትና ለአርሶ አደሩ የተሻሻለ ምርጥ ዘር በማቅረብ እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ  መፃኢ እድልን ብሩህ ማድረግም ይቻላል።

ጊዜ እየነጎደ በሄደ ቁጥር የሰፋፊ እርሻዎች ፍላጎት እየጨመረ ስለሚሄድ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ዲጂታል ቴክኖለጂን በመጠቀም ምርታማነትንና የሰብል ውጤትን ማሳደግ ውዴታቸው ሳይሆን ግዴታቸው ይሆናልም ያለው ሀተታው፤ ደመናን መሰረት ያደረገ ግብርና ፣ሰው አልባ በራሪ አካልን በመጠቀም የሚሰራ ቅድመ ምልከታ፣የስለላ አነፍናፊ መሳሪያ እና ሌሎች የቴክኖለጂ ቁሶችን በመጠቀምና አርሶ አደሮቹ በዲጂታል ቴክኖለጂ እንዲታገዙ በማድረግ ዘወትር የሚገዳደሯቸውን ፈተናዎች በዘመነ የግብርና ዘዴ እንዲያልፏቸው ማድረጉም ቀላል ተግባር እንደሆነ ተጠቅሷል።

ለዚህ ስኬት ግን ግልጽ የግብርና አተገባበር ወይም ወቅቱን የጠበቀና  ሰብልን ፣ ውሃን ፣ ማዳበሪያን ፣ ፀረ አረም እና አፈርን የተመለከቱ መረጃዎችን በመስጠት የአካባቢን ስነ ምህዳር በማይጎዳ ሁኔታ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚቻልም ፀሐፊው ጠቅሷል።

ይሄንን እውን ለማድረግ የሚጠቅሙ መሳሪዎች ደግሞ  የሳተላይት ምስሎች፣ሰው አልባ በራሪዎች፣ነገሮችን የሚያነፈንፉ የኢንተርኔት መተግበሪያዎች እና የመረጃ ትንተና መሆናቸውን ይገልጻል።

በመሳሪያዎቹ በመታገዝም የሚቀርቡትን እውነታዎች አነስተኛ ማሳ ላላቸው አርሶ አደሮች በፍጥነት ማድረሱ ደግሞ ለምርት መጨመር የራሱ በጎ አስተዋጽኦ አለው።

ኢትዮጵያ ባለፉት አስርተ አመታት ስኬታማ በሆነ መንገድ የኢኮኖሚ ስብጥሯን በማሳደግ በአገልግሎት ዘርፉ ፈጣን  እድገት ማስመዝገቧን የገለጸው ጸሐፊው፤ግብርናውን በማዘመንና በማሳደግ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ጤናማ በሆነ መልኩ እንዲጓዝ ለማድረግም እየሰራች ትገኛለች ብሏል።

አገሪቷም በርካታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና ቴክኒኮችን ለመላመድ ያሏትን አማራጮች በመጠቀም የግብርናውን ምርታማነት ማሳደግ ትችላለች፤ በዚህም ወደፊት በአለም አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ ዋና ተዋናይ የመሆን አቅም አላት ብሏል።

ኮርቴቫ አግሪ ሳይንስ የተባለ አለም አቀፍ የግብርና ምርቶች እና መሳሪያዎች  አቅራቢ ኩባንያ እንደሚጠቅሰውም አገሪቷ ይህን የማሳካት እምቅ አቅም አላት።

ኩባንያው የሚያቀርባቸውና በግብርናው ዘርፍ እውቅ፤ የተሰጣቸው አዳዲስ መለያዎች እና በዘርፉ ቀዳሚ የሆኑ ምርቶች እንዲሁም በቴክኖለጂ የበለጸጉ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ለእድገቱ ዋነኛ አጋዥ ናቸው።

ኩባንያው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የምግብ አቅርቦቱን በማሳደግ አምራቾች እና ተጠቃሚዎች  የተሻለ አኗኗር እንዲኖራቸውና ለመጪው ትውልድ እድገትን ለማውረስ በቁርጠኛነት እንደሚሰራ ማስታወቁንም ዘጋቢው ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም