አዲሱ ፓርቲ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመገንባት እንደሚያግዝ አመራሮች ገለጸ

57
ኢዜአ ታህሣስ 7/2012  በውህደት የመጣው አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ በሀገሪቱ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመገንባት እንደሚያግዝ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አመራሮች ገለጹ ፡፡ በብልጽግና ፓርቲ ህገ ደንብና ፕሮግራም ዙሪያ ለዞኑ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቋል ፡፡ ከስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች መካከል  ወይዘሮ ጋዲሴ ሻሾ በሰጡት አስተያየት አዲሱ ፓርቲ በሀገሪቱ ለ27 ዓመታት በስም ብቻ የነበረና በተግባር ግን መሬት ያልነካው  ፌዴራሊዝምን በማስቀረት እውነተኛውን ለማምጣት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ይህም  የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በማስከበር የሀገሪቱ ዜጎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። "የብልጽግና ፓርቲ እውነተኛ ፌዴራሊዝም በመዘርጋት  መልስ ያላገኙ የተለያዩ የብሄር ብሔረሰቦች ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው"  ያሉት ደግሞ በዞኑ የአሙሩ ወረዳ አመራር አቶ ግርማ ኩሣ ናቸው፡፡ አዲሱ ፓርቲ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን ሥልጣን የተነፈጉትን ክልሎች በአንድነት በማቀፍ  እኩል የመሳተፍ  መብት እንደሚያጎናጽፋቸውም አቶ ግርማ አመልክተዋል ፡፡ ሌላው የዞኑ አመራር  አቶ ጀባ አዱኛ በበኩላቸው ፓርቲው በሀገሪቱ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ሥራ ላይ በማዋል የሕግ የበላይነት እንዲከበር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። "ዜጎችን በማቀራረብ  አንድ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ያስችላል " ብለዋል። በሻምቡ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ትናነት በተጠናቀቀው ስልጠና  በዞኑ በየደረጃው ከሚገኙ የአስተዳደር አርከኖች የተወጣጡ ከ300 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች መሳተፋቸውን የዞኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለሊሣ በቀለ ገልጸዋል። ፡ በተመሳሳይ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን  ለተውጣጡ ከ400 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠ መሰጠቱን  የዞኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰበርጋ ሂርጳ  ለኢዜአ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም