በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

73

ኢዜአ፤ታህሰስ 07/2012 የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ወጣቶች ጠየቁ። ወጣቶቹ ይህንን የጠየቁት "ወጣቶች ለሰላም" በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ኃይማኖቶች ጉባኤ በአዳማ ከተማ  ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስ በተካሄደበት ወቅት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ላይ ነው።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን አባል ወጣት ባጫ ጅሬኛ እንዳለው የኃይማኖት አባቶች ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ለሀገሩ ሰላም ዘብ እንዲቆም ማስተማር አለባቸው።

አባቶች ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ ሆነው የመንፈሳዊ መሪነት ሚናቸውን በአግባቡ በመወጣት ተከታዮቻቸው በመልካም ነገር ላይ ማነፅ እንደሚጠበቅባቸው ተናግሯል።

ወጣቱ በማያያዝም “አሁን እያየን ያለነው የሀገር ሽማግሌዎችም ሆኑ መንፈሳዊ መሪዎች መድረክ ላይ ሲወጡ ስለ ፖለቲካ ነው የሚነግሩን” ብሏል።

ወጣቱ ኃይልና ሰፊው ህብረተሰብ በሀገር ሰላምና መረጋጋት ውስጥ የድርሻውን እንዲወጡ  ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቋል።

“ሁላችንም በሰላም መኖር የሚንችለው ከራሳችን ጀምረን ስለ ጎረቤታችን ሰላም ማሰብ ስንችል ነው” ብለዋል።

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወረዳዎች ነዋሪው ልዩነት ሳይገድበው በአንድነት የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ በየደረጃው ያሉ የወጣቶች አደረጃጀቶቻችን እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁሟል።

የእምነት አባቶች ሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች በመድረክ ላይ የሚሉትን መልካም ነገር ወደ ተግባርም በማሸገጋር ማሳየት እንዳለባቸው ያመለከተው ደግሞ በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኝነት ዘርፍ ኃላፊ ወጣት አስማማው ጥጋቡ ነው።

የአብሮነትና የሰላም እሴት ግንባታ ማጠናከር ያስፈልጋል።

ወጣቱ የሰላም ኃይል እንዲሆን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከ4ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ እንዲወያዩ በማድረግ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ውስጥ የድርሻችን እየተወጣ መሆኑን ወጣት አስማማው ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባል ወጣት ሙዲን ናስር በበኩሉ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች የግል ፍላጎትና የፖለቲካ ትርፍ የሚፈልጉ ኃይሎች ተፅእኖ ሥር የመውደቅ ሁኔታ እንደሚስተዋል ገልጿል።

ወጣቶች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ አበክረው በማስተማር አንድነታቸው እንዲጠናከር በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክቷል።

ወጣት ሙዲን “አባቶቻችን ከማንኛውም ተፅእኖ ነፃ ሆኖ ለሰላምና መረጋጋት መስራት አለባቸው “ብለዋል።

በሁሉም ዘርፍ የወጣቶቹ ተሳትፎና የተጠቃሚነት ጉዳይ በመንግስት ትኩረት እንዲያገኝ የኃይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲደግፉም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም