የካሳ ክፍያችን ሳይፈፀም ከይዞታችን ልቀቁ መባሉ ከህግ ውጭ ነው-----የሰቆጣ ከተማ የልማት ተነሽዎች

59
ኢዜአ ታህሳስ 7 / 2012   -የካሳ ክፍያችን ሳይፈጸም ከይዞታችን እንድንለቅ ግፊት መደረጉ ከህግ ውጭ ነው ሲሉ የሰቆጣ ከተማ የልማት ተነሺዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ከልማት ተነሺዎች መካከል እሙሀይ ፀጋየ ሚሰው ለኢዜአ እንደገለጹት ከብልባላ-ሰቆጣ እየተገነባ ባለው የአስፓልት መንገድ ካሳ ሳይከፈል ከይዞታቸው እንዲነሱ ግፊት እየተደረጋገባቸው ነው። ለመንገድ ግንባታው ከሁለት ዓመት በፊት እንዲነሱ 319 ሺህ ብር ግምት እንደሚከፈላቸው ቢገለፅላቸውም ተግባራዊ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል። ከጠቅላላ ግምቱ ውስጥ ባለፈው ዓመት 49 ሺህ ብር ቢከፈላቸውም ቀሪ ገንዘብ ሳይሰጣቸው ቤታቸውን አፍርሰው እንዲለቁ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑንና ይህም ተገቢ እንዳልሆነ  ቅሬታቸውን ተናግረዋል። የካሳ ክፍያው ሙሉ በሙሉ ቢከፈላቸው ከተማ አስተዳደሩ በሰጣቸው ምትክ ይዞታ ቤት ሰርተው ለመኖር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ አቶ ሃብቱ ጌታወይ በበኩላቸው በአስፓልት መንገድ ስራው ምክንያት ለሚነካባቸው ይዞታ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካሳ እንደተገመተላቸው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተገመተላቸው የካሳ ክፍያ ባለመፈጸሙ ከይዞታቸው ለመነሳት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ምትክ መሬት በመስጠት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ቢወጣም በመንገዶች ባለስልጣን በኩል የካሳ ክፍያው ባለመፈፀሙ ምክንያት ከይዞታቸው ለመነሳት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ "የካሳ ክፍያችን እንዳልተፈፀመልን እየታወቀ የከተማ አስተዳደሩ ከይዞታችሁ ልቀቁ ማለቱ ቅሬታ ፈጥሮብናል" ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ በኃይሉ መኮንን በበኩላቸው በልማት ተነሺዎች የተነሳው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል፡፡ በብልባላ-ሰቆጣ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት 223 ባለይዞታዎች ለበርካታ ጊዜያት የካሳ ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ እንደምክትል ከንቲባው ገለጻ ከተማ አስተዳደሩ ለባለይዞታዎቹ ተለዋጭ መሬት የማቅረብ ኃላፊነቱን ቢወጣም በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ለባለይዞታዎች ካሳ ሙሉ በሙሉ መክፈል ባለመቻሉ ቅሬታው ተፈጥሯል። የአስፓልት ሥራ ፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ጊዜ በመቃረቡና የከተማው ይዞታ ካልተከበረ የመንገድ ሥራው ሳይከናወን እንደሚቀር መንገዶች ባለስልጣን በመግለጹ ለባለይዞታዎች ንብረታቸውን እንዲያነሱ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡ በህብረተሰቡ የተነሱ ቅሬታዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ከባለይዞታዎችና ከመንግስት የተዋቀረ ኮሚቴ በካሳ ክፍያ እንዲፈፀም ላይ ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር እየተወያዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የመንገዶች ባለስልጣን ጉዳይ አስፈፃሚ ኮሜርሻል ኖሚንስ ደሴ ቅርንጫፍ ገንዘብ ያዥ የሆኑት ወይዘሮ ህይወት ይማም የልማት ተነሺዎቹ ቅሬታ አግባብ መሆኑን በስልክ ለኢዜአ ገልጸዋል። ለሰቆጣ ከተማ የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ የዘገየው በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ገንዘቡ ባለመግባቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። "በዚህም ከመንገዶች ባለስልጣን በኩል ገንዘቡ እንደተለቀቀልን ሰቆጣ ከተማ ድረስ በመሄድ ክፍያውን እንፈፅማለን" ብለዋል፡፡ የብልባላ-ሰቆጣ የአስፓልት መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ከ98 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚሸፍን ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም