የፓርቲው ማህበራዊ መሰረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል---አመራሮች

96
ኢዜአ ታህሳስ 7 /2012   የብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ መሰረቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያቀፈ በመሆኑ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የፓርቲው አባላት ተናገሩ፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም፣ ህገ-ደንብና የህዝብ ግንኙነት ሰነዶች ላይ ተወያይተዋል። የከተማ አስተዳደሩ የአዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ እንደተናገሩት ብልጽግና ፓርቲ ለወጣቶች፣ ለአርብቶ አደሮች፣ ለአርሶ አደሮችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ማህበራዊ መሰረቶቹ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውንና የፓርቲው የፖለቲካል ኢኮኖሚ መርህም እያደገ መሄድን የሚከተል መሆኑን አስረድተዋል። ፓርቲው አቅርቦት መር ኢኮኖሚን እንደሚከተል የገለጹት አቶ ሞላ ሀብት ማፍራትን፣ ምርት ማሳደግና የሥራ እድል ፈጠራ ላይ አተኩሮ ስለሚሰራ ልማትን እንደሚያፋጥን ተናግረዋል፡፡ እንደኃላፊው ገለጻ ፓርቲው በድሃና በሀብታም መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማሴ በበኩላቸው በብልጽግና ፓርቲ መርህ መሰረት ኢኮኖሚው በግሉና በመንግስት ሴክተር ጥምረት ይመራልው። "በመሆኑም ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪንና ሳይንስና ቴክኖሎጅን በጥምረት በማካሄድ የመላ ህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት አድርጎ ይሰራል" ብለዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት መንግስት በግል ሴክተሩ እንደፈለገ ጣልቃ የሚገባ ሳይሆን በግሉ የማይሸፈኑ የኢኮኖሚ አማራጮችን በመሸፈን የህዝብ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል፡፡ "ፓርቲው ለህግ የበላይነትና ለሰላም ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ ዜጎች ለልማት ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋል" ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ አለበል አለሙ ናቸው፡፡ ርዕዮተዓለም የህልውና ጉዳይ ነው ብሎ የማይነሳ በመሆኑ የተሻለ አስተሳሰብ ካለ ከፓርቲው ፕሮግራሞችና ህገ-ደንቦች ጋር አጣጥሞ እንደሚሄድ አስታውቀዋል። በውይይት መድረኩ ላይ ከ250 በላይ የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የክፍለ ከተማ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በቀጣይም በአባላት ላይ ግልጽ ግንዛቤ ለመፍጠር እስከክፍለ ከተማና ቀበሌ ድረስ ውይይቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም