ቢሮው አዲሱን የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ በማይተገብሩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

103
ኢዜአ ታህሳስ  7/2012  አዲሱን የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በፍጥነት ተግባራዊ በማያደርጉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የእርምት እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የሶማሌ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች በአዋጁ አተገባበርና ያጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ በጅግጅጋ ከተማ ተወያይተዋል ። የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ 621 ∕ 2001 ተሻሽሎ 1113 ∕ 2011 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመባል መውጣቱ ይታወቃል። አዲሱ አዋጅ  ከደነገጋቸው ጉዳዮች አንዱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በማህበረሰቡ ስም ከሚያገኙት ገንዘብ 80 በመቶውን ለፕሮጅክቶች ማስፈፀሚያ ቀሪውን ደግሞ ለቢሮ አገልግሎት እንዲያውሉ የሚያስገድድ ነው። ድርጅቶቹ በሀገር ወሰጥ ሊገኝ ካለቻለ በስተቀር ፕሮጀክቶቻቸው በሚተገበሩበትና ቢሮዎቻቸው ባሉባቸው  አካባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች የስራ ቅጥር ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚለውም ሌላው በአዋጁ የተደነገገ አስገዳጅ ሁኔታ መሆኑን የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገልጸዋል። የቢሮው  ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲከደር መሐሙድ በወቅቱ እንዳሉት  በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአዋጁ ይዘትና አተገባበር ዙሪያ ከሶስት ወር በፊት ስልጠና ተሰጥቷል ። "ይሁንና በክልሉ እየተንቀሳቀሱ ያሉ መንግሰታዊ ድርጅቶች በአዋጁ መሰረት እየሰሩ አይደለም " ብለዋል ። ድርጅቶቹ መንግሰታዊና መንግሰታዊ ካልሆኑ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች የሚያገኙትን በጀት በትክክል ለህዝብ ጥቅም ስለማዋላቸው የሚገልፅ ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻሉም ጠቅሰዋል። የድርጅቶቹ ተቀጣሪ ሰራተኞችም ከክልሉ ውጭ ያሉ መሆናቸውን አመላክተዋል። በሮው ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በመተባበር በአዋጁ መሰረት ስራቸውን በማያከናወኑ ድርጅቶች ላይ የማስጠንቀቂያና የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል። "ድርጅቶቹ ከዝቅተኛ እሰከ ከፍተኛ የሰራ መደቦች የሰራተኛ ቅጥር የሚያካሄዱት ከክልሉ ውጭ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰዲቅ አብዲቃድር ናቸው። "በዚህም ህብረተሰቡ ከድርጅቶቹ ማገኘት የሚገባውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በአግባቡ እያገኘ አይደለም " ብለዋል ። ድርጅቶች መስፈርቱን ለሚያሟሉ የክልሉ ወጣቶች የስራ እድል ሊፈጥሩ እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል። የክልሉ የፋይናንና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፋንድ አሰባሰብ ስራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ አብዲቃድር መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ 64 ሀገር በቀል፣ 41 ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሉ ገልጸዋል ። ድርጅቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል እንስሳት እርባታ፣ ትምህርት፣ ጤናና ንጹህ መጠጥ ውሃ ልማት እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በውይይቱ ከተሳተፉ መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች መካከል አንዳንዶቹ መስሪያ ቤቶቻቸው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ በመሆናቸው አዋጁን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር አለመቻላቸውን ተናግረዋል። እንደአውሮፓ አቆጣጠር  በ2020 በጀት ዓመት ጀምሮ በአዋጁ መሰረት ስራቸው እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም