የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ለሴካፋ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ይወዳደራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ለሴካፋ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ይወዳደራሉ
75
ኢዜአ ፤ታህሳስ 7/2012 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሆን ይወዳደራሉ። ሴካፋ ነገ በዩጋንዳ ካምፓላ በሚያደርገው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለቀጣይ አራት ዓመታት ሴካፋን የሚመሩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ይመረጣሉ። በዚሁ ምርጫ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሆን ከሌሎች እጩዎች ጋር ይወዳደራሉ። አቶ ኢሳያስ ለምርጫው የሚያስፈልገውን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው በምርጫውና በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማለዳውን ወደ ካምፓላ ማቅናታቸውን ፌዴሬሽኑ ገልጿል። አንድ አገር እጩ ለማቅረብ ዓመታዊ የሴካፋ የአባልነት ክፍያ መክፈል እንደሚጠበቅበትና ይሄንንም ኢትዮጵያ እንደምታሟላ ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አቶ ኢሳያስ የሴካፋ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ የሴካፋ አባል አገሮች ከምክር ቤቱ እኩልና ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት ይሰራሉ። እንዲሁም የቀጠናውን እግር ኳስ እድገት የሚያመጡ ስራዎችንም ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም የህዝብ ግንኙነት ዳትሬክተሩ አመልክተዋል። ሴካፋ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ከፕሬዚዳንትና ከምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫ ባለፈ በተጓደሉ የምክር ቤት አባላት ምትክ ምርጫ ያካሄዳል። በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባኤው በሴካፋ ወቅታዊ የእግር ኳስ ሁኔታና እድገት አስመልክቶ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።