የኢትዮጵያ የባህል ቡድን አስመራ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

75
ኢዜአ፤ታህሳስ 6/2012 በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት የተመራው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን ታህሳስ 6 ቀን 2012 ዓም ከስዓት በኋላ አስመራ ገብቷል። ቡድኑ አስመራ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ በኤርትራ የባህል እና ስፖርት ኮምሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክሌ፣ በኤርትራ የኢፌዲሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር አርዓያ ደስታ፣ ታዋቂ የኤርትራ አርቲስቶች፣ የኤርትራ የሴቶች ማህበር እንዲሁም ሌሎች የስራ ኃላፊዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ከ60 በላይ አባላትን የያዘው የባህል ቡድን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከታዋቂ ድምጻዊያንና የጃኖ ባንድ የተካተቱበት ሲሆን ለአንድ ሳምንት በኤርትራ ይቆያል። የባህል ቡድኑ የኤርትራ ጉዞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው። የውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው የባህል ቡድኑ በኤርትራ ቆይታው በአስመራ፣ ከረን እና ምጽዋ ከተማዎች የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። የኤርትራ የባህል ቡድን ባለፈው የካቲት ወር 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህርዳር እና በሀዋሳ ከተማዎች ማቅረቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም