በአገሪቷ ህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ምክር ቤታችን ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር አብሮ ይሰራል-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

77
ኢዜአ ታህሳስ 6/2012 በአገሪቷ ህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍንና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ከሌሎች የዕምነት ተቋማት ጋር አብሮ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ከታህሳስ 1 እስከ 4 ቀን 2012ዓ.ም ያደረገውን የምክር ቤቱን አንደኛ መደበኛ ጉባኤ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የተጀመረውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ አንድነት በማጠናከር በኩል የሚቻለውን ሁሉ እንደሚደረግና በየክልሉ መጅሊሶችን በአዲስ መልክ የማዋቀሩ ስራም እንደሚቀጥል የኡለማ ምክር ቤቱ ዋና ፀሃፊ ሼህ ቃሲም መሃመድ ታጁዲን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል። የጠቅላላ ጉባኤውን እና የስራ አስፈፃሚ አመራር አባላት የውስጥ የመተዳደሪያ ደንብንና የአመራሩን አሰራር ለማዘመንም ውሳኔዎች መወሰናቸውንም እንዲሁ። በቡድንተኝነትና በስረዓት አልበኝነት ስሜት የመስጂድ ኢማሞችንና የመድረሳ አስቀሪዎችን የማፈናቀል ተግባሮች ሰላምን የሚያውኩ በመሆናቸው ያንን ለመከላከል የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች በጋራ እንደሚሰሩም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ምክር ቤቱ በስብሰባው አገራዊ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች አንድነትና ሰላምን አስመልክቶ ባለ 17 የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን ከዚህ ውሰጥ በሃይማኖት ተቋማትና አማኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከልን አጽንኦት ሰጥተውታል። ይህን በተመለከተም ምክር ቤቱ በእስልምናና በሌሎች የእምነት ተቋማት እንዲሁም አማኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን ጉዳዩ ሁሉንም ህዝብ ሊያሳስበው የሚገባና ሊቆም የሚገባ መሆኑም ተገልጿል። በተለይም በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ ምክንያት ጥላቻና መከፋፈል እንዳይፈጠር በሰላምና ደህንነት፣ በህዝቦች መቻቻል፣ በመተማመን፣ በፍቅር እና አንድነት ላይ ለመስራት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም በአቋም መግለጫው አስቀምጧል። ምክር ቤቱ ሚያዝያ 23 ቀን 2011ዓ.ም  ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እንደሚያፀናና በትግበራ ላይ የታዩ ክፍተቶችን በማረም የህዝበ ሙስሊሙን አንድነትና ሰላም ለማስከበር ለሁሉም በእኩልነትና በግልፀኝነት እንደሚሰራም አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም