የሁመራ የቁም እንስሳት ጤንነት መመርመሪያ ማዕከል ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ

53
ኢዜአ ታህሳስ 6  2012 --- በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የሚላኩ የቁም እንስሳት ጤንነትን መመርመሪያ ማዕከል ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ። ማዕከሉን ለመገንባት መንግስት 60 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተመልክቷል። የሁመራ የቁም እንስሳት ጤንነት መመርመሪያ ማዕከል (ኳራንታይን) አስተባባሪ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ በቀን 6ሺህ የቁም እንስሳትን በመመርመር የጤንነት ማረጋገጫ ሰርቲፍኬት ፍቃድ የመስጠት አቅም አለው፡፡ ማዕከሉ ሱዳንን ጨምሮ ወደሌሎች አገሮች ለሚላኩ የቁም እንስሳት አገልግሎት በመስጠት በወር 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የወጭ ምንዛሬ እንዲያስገኝ ታስቦ የተገነባ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ለ50 ቋሚና ለ200 ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ150 ሺህ በላይ የቁም እንስሳት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ተሻግረዋል። በእዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማጣቷን ጠቅሰው ማዕከሉ በተሟላ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጥ ለህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የቁም እንስሳት ንግድ ህጋዊ በሆነ መንገድ መጀመር ከእንስሳት ተቀባይ አገራት ጋር የንግድ ትስስር እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ በማዕከሉ የእንስሳት ባለሙያ አቶ ብርሀነ ጸሐየ ናቸው፡፡ በተለይ ወደ ሱዳን፣ ሊቢያና ሳዑዲ ዓረብያ ለሚደረገው የቁም እንስሳት ንግድ  የሁመራ ኳራንታይን ማዕከል አመቺ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ "ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የተዘጋጀው ማዕከል ህገ-ወጥ የእንስሳት ንግድን ለማስቆም ይረዳል" ብለዋል፡፡: አቶ ብርሃነ እንዳሉት በዘርፉ የተሰማሩ የሱዳን ባለሀብቶች ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃውን የእንስሳት መመርመሪያ ማዕከል በቅርቡ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡: የዞኑ የግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋይ የዕብዮ በበኩላቸው አካባቢው ለእንስሳት ሀብት እርባታና ማድለብ ሥራ አመቺ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህገ-ወጥ የእንስሳት ዝውውርን ለመቆጣጠር የማዕከሉ አገልግሎት መጀመር መልካም መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ በዞኑ ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ የእንሳት ሀብት እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል ሲል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም