በመተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻልንም - ተገልጋዮች

80
መተማ ሰኔ 15/2010 የመተማ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ባለመጠናቀቁ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ የገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አቶ የማታው ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለፁት የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ግንባታ ሲጀመር የተሻለ ህክምና የማግኘት ተስፋ ነበራቸው፡፡ ሆኖም ግን ግንባታው ከተጀመረ አራት አመት ቢሆነውም ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ በሆስፒታሉ ማግኘት የሚገባቸውን ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ጎንደር  በሚያደርጉት ጉዞ ለከፍተኛ ወጭና እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለህመማቸው ረጅም ክትትልና ተኝተው መታከም እንዳለባቸው በባለሙያዎች ቢታዘዝም በአልጋ እጦት መከታተል እንዳልቻሉ የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ካሰኝ በለጠ ናቸው። በዚህም ምክንያት ወደ ጎንደር ሆስፒታል በመሄድ ለተጨማሪ ወጭና እንግልት መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ የሆስፒታሉ ተወካይ ስራ አስኪያጅ አቶ በፈቃዱ ቀስቅስ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ለተገልጋዩ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ከአራት አመት በፊት የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ የማስፋፊያ ግንባታው በ2006 ዓ.ም ሀምሌ ወር ላይ ተጀምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ውል የተገባ ቢሆንም በተቋራጩ ችግር ምክንያት መጠናቀቅ ከነበረበት በሁለት ዓመት መጓተቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የቀዶ ህክምናን ጨምሮ ታካሚዎችን አስተኝቶ ማከም አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ሆስፒታሉ ደረጃውን በማሳደግ የተሻለ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን የጤና ባለሙያዎችንና የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ለማስገባት የያዘውን እቅድ ማሳካት እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡ ይህም በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ከተቋራጩ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም የተለያዩ ስበቦችን በማምጣት ሊያጠናቅቀው አለመቻሉንና ግንባታውን ማቋረጡን ተናግረዋል። የማስፋፊያ ግንባታው አሁን 67 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ከተቋራጩ ጋር የነበረውን ውል በማቋራጥ ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠት በክልሉ ጤና ጥበቃ በኩል ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው የማስፋፊያ ግንባታው መጓተት ሆስፒታሉ መስጠት ያለበትን አገልግሎት ካለመስጠቱ በተጨማሪ በተገልጋይ ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡ የግንባታው መጓተት ዋነኛ ችግርም የግንባታ ተቋራጩ ድክመት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት ከ90 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማውና አካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስገንዝበዋል። ለማስፋፊያ ግንባታው ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 51 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ እንደነበር ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም