ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ 251 ህገ ወጥ የቱርክ ሽጉጥ ተገኘ

69
ኢዜአ ታህሳስ 6 ቀን 2012 በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ 251 ህገ ወጥ የቱርክ ሽጉጥ መገኘቱን የወረዳው አስተዳደር ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ እሸቱ ስመኘው ለኢዜአ እንደተናገሩት ህገ-ወጥ ሽጉጡ የተገኘው ዛሬ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ ለፍተሻ በተሰማሩ የፀጥታ አካላት ነው። ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት  ሲሞክር የተገኘው ሽጉጡ በኤፍ ኤስ አር የጭነት መኪና ላይ ለህገ-ወጥ ስራ እንዲያገለግል ታስቦ በረቀቀ መንገድ በተሰራ ሳጥን ውስጥ እንደሆነ ተመልክቷል። የመኪናውን አሽከርካሪ የፀጥታ አካላት ደርሰውበት  የጦር መሳሪያው አራግፈው እንዳበቁ ሊይዙት ሲሉ መኪናውን አስነስቶ ቢያመልጥም ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ለሀገሪቱ  ሰላም ስጋት መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡ መሰል ህገ ወጥ ድርጊትን ለመቆጣጠር ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡ በወረዳው ትናንትም 16 ክልሽንኮቭና ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ጥይት  በህገ ወጥ መንገድ  ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ መያዙን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም