የአማራና ኦሮሞ ፖለቲከኞች በክልሎቹ ሕዝቦች የጋራ መስተጋብር ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ተጠየቀ

102

ኢዜአ፤ታህሳስ 6/2012 በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች በልዩነቶች ላይ ከመነታረክ ወጥተው የሁለቱን ሕዝቦች የጋራ መስተጋብር በሚያጎሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንዲሰሩ ተጠየቀ።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልልች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ በጋራ እየመከሩ ነው።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት፣ የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች የአብሮነት ታሪክና  መጻኢ ዕድል ላይ ውይይት ይደረጋል።

መድረኩ ቀደም ሲል የሁለቱን ሕዝቦች አብሮነት አስመልክቶ የተካሄዱ ውይይቶች አካል መሆኑ ተገልጿል።

አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በዛሬው መድረክ የመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፤ አማራና ኦሮሞ እንዳይነጣጠሉ ሆነው በደምና ስጋ የተሳሳሩና በርካታ እሴቶችን የሚጋሩ ሕዝቦች ናቸው።

ሁለቱ ሕዝቦች ለአገር ግንባታ በጋራ ዋጋ እንደከፈሉ ሁሉ በሂደቱ ቁርሾ የፈጠሩ ክስተቶች ነበሩ ብለዋል።

የበርካታ አገራት የሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት መሰል ታሪክ ማስተናገዱን በማስታወስ።

ሕዝብን በማንቃት ደረጃ ቀዳሚ የሚባሉት የፖለቲካ ኃይሎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ቀድመው ባለመወጣታቸው ችግሩ ተባብሶ ለሰው ሕይወት መጥፋት መንስኤ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች በጥላቻ አዙሪት ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉንም አውስተዋል።

በመሆኑም ፖለቲከኞች የእነዚህን ሕዝቦች ልዩነት እየለቀሙ ከመነታረክ ወጥተው በጋራ መስተጋብሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር /ኦነግ/ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በተለይ ወጣቶችን የማጋጨቱ ስራ እየሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ሕዝብን ከማጋጨት ወጥቶ ወደ ሰለጠነ የሃሳብ የበላይነት ትግል መሸጋገር እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉ አብዛኞቹ የፀጥታ ችግሮች በሁለቱ ክልሎች መሆኑን ጠቅሰው፤ እየተካሄደ ያለው መድረክ በዋናነት እነዚህን ችግሮች መፍታት ላይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል።

መድረኩ ከአማራና ኦሮሞ በተጨማሪ ሌሎች ሕዝቦችን ያቀፈ አገራዊ ውይይት የመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሁለቱ ክልሎች ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲልም አንድነትን ማጠናከርና ሠላም ማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ሰባት ፓርቲዎችም በክልሎቹ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም