ወጣቶች ዋጋ ከፍለው ያመጡትን ለውጥ የፖለቲካ ልሂቃን በሰከነ መንፈስ መምራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

84
ኢዜአ፤ ታህሳስ 6/2012 ወጣቶች ዋጋ ከፍለው ያመጡትን ለውጥ የፖለቲካ ልሂቃን ከፉክክር ወጥተው በሰከነ መንፈስ መምራት እንዳለባቸው ተጠቆመ። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ዋነኛ ምክንያታቸው በፖለቲካ ልሂቃን መካካል በሚፈጠር ሽኩቻና ፉክክር መሆኑም ተነግሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልልች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የሁለቱ ህዝቦች የጋራ አብሮነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ በጋራ እየመከሩ ነው። በምክክር መድረኩ በሁለቱ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ አንጋፋና ወጣት የፖለቲካ ልሂቃኖች በተጨማሪ አክቲቪስቶችም ተሳታፊዎች ናቸው። ኢዜአ መድረኩን አስመልክቶ አክቲቪስት ጃዋር መሀመድንና የአማራ ማህበራዊ ራእይ ግንባር ፕሬዚዳንት አቶ ስዩም መንገሻን አነገጋግሯል። አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ እንዳሉት፤ በአማራና ኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች  ዋነኛ ምክንያት የፖለቲካ ልሂቃን የሚፈጥሩት ያልተገባ ፉክክር ነው። በመሆኑም ፓለቲከኞች የዴሞክራሲ ሜዳ መጫዎቻ ህጉ ላይ በመነጋጋር መስማማት እንዳለባቸው አመልክተዋል። "ከዚህ አንጻር  በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳሱ የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ መወያየት መጀመራቸው ከሁለቱ ህዝቦች ቁጥር አንጻር ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ፋይዳ አለው" ብለዋል። ሁለቱ ህዝቦች ዘመናትን የተሻገረ አብሮነት እንዳላቸው በመጠቆም። አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ የህዝቦች ፍላጎት ተመሳሳይነት እንዳለው ገልጸው፤ የፖለቲካ ልሂቃን እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት በጋራ መነጋጋር እንዳለባቸው አመልክተዋል። ይህ መሆን ካልቻለ ግን በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለው የእርስ በርስ  እይታ የተዛባና ጥርጣሬ የተሞላበት ይሆናል ነው ያሉት። በልሂቃኑ መካከል የሚደረገው ምክክር የግድ አንድ አይነት አቋም ለመያዝ መሆን እንደሌለበትም ገልጸዋል። ''ፍርሃትና ጥርጣሬ በተሞላበት ግንኙነት አገር መገንባት አይቻልም'' ያሉት አቶ ስዩም፤ የኦሮ-ማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክርም ይህን ችግር በመፍታት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል። በቅርቡ በኦሮሚያና አማራ  ክሎች ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የንጹሃን ተማሪዎችን ህይወት ማለፉ ይታወሳል። ጉዳዩን በሚመለከት የሁለቱ ክልሎች ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ በጋራ መክረዋል። ይሁንና የጋራ መድረኩ እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ በሚገባው ደረጃ ባለመውረዱ የሚጠበቅበትን ያህል ስኬት አለማስመዝገቡን የሚናገሩ ሰዎች አሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም