የኢትዮጵያና የጂቡቲ የባለሙያዎች ቡድን የአገሮቹን ኢኮኖሚያዊ ውህደት በሚያፋጥኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ

57
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 የኢትዮጵያና የጂቡቲ የባለሙያዎች ቡድን የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ውህደት በሚያፋጥኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ የሆነ ውይይት አድርጓል። አገሮቹ እ አ አ በ2016 በአዲስ አበባ ባደረጉት 14ኛው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማሳደግ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል። ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው የሁለቱም አገሮች ባለሙያዎች ውይይትም የነዚህ ስምምነት አፈጻጸምና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ለመገምገም ነው። በስምምነቶቹ ዙሪያ የተደረገው የባለሙያዎች ውይይት  ውጤታማ እንደነበር በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገሮችና የኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር መሀመድ ድሪር ተናግረዋል። ውይይቱ ለሁለቱም አገሮች ህዝቦች የተሻለ ጥቅም ለማስገኘት፣ የኢኮኖሚ ውህደት ለማሳደግና በቀጠናው አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር የሚያግዝ ነው። በፖለቲካ፣ በደህንነትና በኢኮኖሚ ዘርፎች ጥሩ የሚባል አፈጻጸም መታየቱን  የገለጹት አምባሳደሩ፤ "በትራንስፖርት ዘርፍ  የታየው አፈጻጸም ግን በሚፈለገው ደረጃ አይደለም" ብለዋል። የትራንስፖርት ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ሁለቱም አገሮች ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ጠቁመዋል። ከተጠቀሱት ዘርፎች በተጨማሪ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አብሮ መስራት እንዲችሉም በባለሙያዎች ተነስቷል። በጂቡቲ የሁለትዮሽ ግንኙነት ኃላፊ ያሲን ሁሴን ዱዋሎ በበኩላቸው ሁለቱም አገሮች ከጥንት ጀምሮ የቆየ ታሪክና ወዳጅነት ያላቸው ናቸው። ድንበር ተሻጋሪ ወዳጅነታቸው አሁን ላይ የኢኮኖሚ ትስስሩም ጠንካራ ደረጃ ላይ መድረሱንም ገልጸዋል። የባለሙያዎቹ ቡድን ውይይት በቀጣይ ለሚካሄደው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ  ግብአት የሚሰጥ እንደሆነ አንስተዋል። 15ኛው የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በጂቡቲ እንደሚደረግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም