የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከኃላፊነት ለመነሳት መልቀቂያ አቀረቡ

100
ሀዋሳ ሰኔ 15/2010 የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በፈቃዳቸው ከኃላፊነት ለመነሳት የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን አቀረቡ። አስተዳዳሪው አቶ ፈቱ ሰማን ለኢዜአ እንደገለጹት የስራ መልቀቂያውን ያስገቡት በአካባቢው የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ  ነው። በኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የከተማ ዘርፍ ድርጅት ሃላፊ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት አስተዳዳሪው መጋቢት 2/2010 ነው በዞን አስተዳዳሪነት የተመደቡት። ምደባው በተደጋጋሚ ይከሰት የነበረውን የአካባቢውን ግጭት ለማረጋጋት ሃላፊነት ጭምር የነበረው ቢሆንም ችግሩን ለማረጋጋት የተሰራው ስራ ውጤታማ አልነበረም ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታው ከሳምንት በፊት ለክልሉ መንግስትና ለመሪው ድርጅት ደኢህዴን ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል። ጥያቄያቸው በክልል መንግስት ምላሽ እንዳላገኘና ርዕሰ መስተዳድሩ የአካባቢው ሰላም እሲኪረጋጋ መቆየት እንዳለባቸው መወሰናቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በቅርቡ በደቡብ ክልል ግጭት በተከሰተባቸው ዞኖች ወረዳዎችና ከተሞች ያሉ አመራሮች በገዛ ፍቃደቸው ስራቸውን መልቀቅ አለባቸው የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ  አቅጣጫ ጥያቄያቸውን በድጋሚ እንዲያቀርቡ አድርጎዋቸዋል። በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ በቅንነት በመቀበል በገዛ ፍቃደቸው ስራቸውን ለመመልቀቅ ወስነው ዛሬ ሰኔ 15/2010 መልቀቂያ አስገብተዋል። ቦታቸውን የሚተካ አካል እስኪመደብ በሃላፊነታቸው እንደሚቆዩ አቶ ፈቱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም