የብስክሌት ውድድር በድሬደዋ ከተማ ተካሄደ

81

 ኢዜአ ታህሣሥ 5/2012 ሠላምና ፍቅር ለድሬ፤ ከትራፊክ አደጋ ሁሉም ራሱን ይጠብቅ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የብስክሌት ውድድር ዛሬ በድሬደዋ ከተማ ተካሄደ። የድሬዳዋ የቀድሞ ብስክሌተኞችና ተተኪዎች የተሳተፉበት የከፍተኛ ኮርስ የሣይክል ውድድር በከዚራ ዋናዋና አደባባዮች በተካሄደበት ወቅት በአስተዳደሩ እየጨመረ የመጣው የተሽከርካሪ አደጋ ለመቀነስ እና የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል የሚያግዝ ትምህርታዊ መልዕክት ተላልፏል፡፡

15 ዙሮች በሸፈነው የከፍተኛ ኮርስ የብስክሌት ውድድር አሚር ጃፋር፣ አክረም ከድርና ተሰቲ ዩሱፍ ተከታትለው በመግባት ያሸነፉ ሲሆን የተዘጋጀላቸውን የገንዘብና የምስክር ወረቀት ከአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህና ሌሎች አመራሮች እጅ ተቀብለዋል፡፡

በዚህ ወቅት ምክትል ከንቲባው “በድሬዳዋ ተከስቶ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት ተወግዶ አንጻራዊ ሰላም እየነፈሰ ይገኛል “ብለዋል፡፡

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጠናከርና የድሬዳዋ ገጽታ እያበላሸ የሚገኘውን የተሽከርካሪ አደጋ ለመቀነስ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሁሉም ተረባርቦ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንዲጠበቅ አዲስ አበባ የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ድሬዳዋ በመምጣት ለፈጠሩት የህዝብ ንቅናቄ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አስተዳደሩ ለዘላቂ ሰላም መጠናከር የህግ የበላይነትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተው የቀድሞ የድሬዳዋ የብስክሌት ስፖርት ዳግም እንዲያሰራራና ከተሽከርካሪ አደጋ የነጻ ካባቢ ለመፍጠር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

“ስፖርትና ሰላም አይነጣጠሉም፤ ነገ ታዋቂውን የቀድሞ የድሬዳዋ አለም አቀፍ ብስክሌተኛ ጀማል ሮጎራ በመተካት ድሬዳዋንና ሀገራችንን ማስጠራት የምንችለው ሰላም ሲረጋገጥ ነው “ያለው የውድድሩ አሸናፊ ወጣት አሚር ጃፋር ነው፡፡

ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ለሰላም ዘብ መቆም አስፈላጊነት እንደሚያስተምርም ገልጿል፡፡

የድሬዳዋ ብስክሌት ፈዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ጀማል ሮጎራ “የሁሉም ነገር መሠረት፤ የረዥም ራዕይ ስኬት መነሻና መድረሻ ሰላም በመሆኑ ስፖርተኞችን ጨምሮ ሁሉም ለሰላም መረጋገጥ መረባረብ አለባቸው “ብለዋል፡፡

በፌደራል ትራስፖርት ባለሥልጣን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመንገድ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ገቢሣ የተሽከርካሪ አደጋ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለማስቆም አመራሩ በጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዛሬ በስፖርታዊ ውድድር የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ በበኩሉ ወጣቱ የነገውን ፍሬ ለማጣጣም ለሰላም ሁሉጊዜም ዘብ መቆም እንዳለበት መልዕክቱን አስተላልፈዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም