የሜጀር ጀኔራል ሓየሎም አረአያ መታሰቢያ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

70
ኢዜአ ታህሳስ 5/2012 19ኛው የሜጀር ጀኔራል ሓየሎም አረአያ መታሰቢያ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዛሬ በክልል ደረጃ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ተካሄደ። አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር በሸፈነው ውድደር ከክልሉ አስራ ሁለት ወረዳዎችና ከስድስት ክለቦች የተውጣጡ ከሁለቱም ፆታዎች ከ200 በላይ አትሌቶች መሳተፋቸውን  የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪዳነ ተክለሃይማኖት ገልጸዋል። በሴቶች በተካሄደው የሩጫ ውድድር ምህረት ተፈራ ከኮረም ወረዳ አንደኛ ስትወጣ ተክለ ካህሳይና መብራት ገደይ በቅደም ተከተል ከአፅቢ ንበርታና ከእምባላጀ ወረዳዎች ተከታትለው ገብቷል። በወንዶች ደግሞ ካህሳይ አፅብሃና ሓፍቶም አባዲ ሁለተም ከሳእሲእ ፃእዳ እንባ ወረዳ አነደኛና ሁለተኛ ሲወጡ ሦስተኛ ከእንደርታ ወረዳ ሓለፎም ተስፋይ ሆነዋል። በክለብ ደረጃ በተመሳሳይ ርቀት በተካሄደው ውድድር ደግሞ ገብሩ አብርሃ፣ሙሩፅ ውበትና ፅላሎም ክንደያ ሁሉም ከጉና የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተከታተለው በመግባት አሸናፊ ሆነዋል። በሴቶች ክለብ ደግሞ ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር ከጉና አንደኛ ስትወጣ ደባሽ ከላላና ዘነቡ ወልደሰነበት ከሱር ክንስትራክሽንና ከዋልታ ፖሊስ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ ውጥቷል። አንደኛ ለወጡ አትሌቶች እያንዳንዳቸው ሃያ አምስት ሺህ ብር ሁለተኛ ለወጡ አሥራ አምስት ሺህ እንዲሁም ሦስተኛ ሆነው ለጨረሱት አሥር ሺህ ብር ተሸልመዋል። የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሩን ብዛት ላቸው የሽሬ እንዳስላሴ ከተማና አካባቢው ስፖርት አፍቃሪ የህብረተሰብ ክፍል ተከታትለውታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም