የምገባ ፕሮግራሙና ድጋፉ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ አግዟል

64
ኢዜአ፤ ታህሳስ 5/2012 በአዲስ አበባ በትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራና ሌሎች ድጋፎች ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማገዙን ኢዜአ ያነጋገራቸው መምህራንና ተጠቃሚ ተማሪዎች ተናገሩ። በድጋፍ ዕጦት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ምግባው በመጀመሩ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንደቻሉና እየተሰጠ ያለው ድጋፍ ለራሳቸውም ሆነ ለወላጆቻቸው እፎይታ በመሥጠቱ ከሀሳብ ነጻ ሆነው በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉንም ነው ተማሪዎቹ የሚገልጹት። በኒው ኤራ የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርት ቤት የ8ኛ  ክፍል ተማሪ ቃልኪዳን ኤርሚያስ   ምግባው  ከመጀመሩ በፊት ቁርስ ሳትመገብ ወደ ትምህርት ቤት ትመጣ እንደነበር አስታውሳ፤  በረሃብ ስሜት ውሰጥ ሆና ትምህርቷን  ለመከታተል  ትቸገር እንደነበር ነው የገለጸችው። የምገባ ፕሮግራሙ ከተጀመረ ወዲህ ግን የትምህርት ፍላጎቷ እየጨመረ መምጣቱንና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀቷን ተናገራለች፡፡ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ያቆብ ደጉ በበኩሉ የእተደረገለት ያለው ድጋፍ ለወላጆቹም ሆነ ለእሱ  ችግሩን እንዳቃለለት ገልጾ፤ ከዚህ በፊት ቤቱ እሩቁ  በመሆኑ እንዳይረፍድበት ቁርሱን ሳይበላ ወደ ትምህርት ቤት ስለሚመጣ ትምህርቱን ለመከታተል  ሲቸገር እንደቆየ ይናገራል። ከሱሉልታ-አዲስ አበባ  ተመላልሶ ስለሚማር ከዚሀ በፊት ከርቀቱ የተነሳ ጠዋት ቁርስ ሳይበላ  ይመጣ  እንደነበር የተናገረው ሌላው ተማሪ ቃለአብ ማሞ፤መስከረም ሲመጣ ወላጆቹ የደንብ ልብስ ና  የትምህርት ቁሰቁስ ለማሟላት ይጨናነቁ  እንደነበር አስታውሶ በዚህ ዓመት የተጀመረው ድጋፍ እፎይታን ሰጥቶናል ብሏል።፡፡ ባለፈው አመት የምግብ ና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የሚያደርግለትን ሰው በማጣት ትምህርቱን ለማቋረጥ መገደዱን የተናገረው በአጼ ልብነ ድንግል አጸደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሲሳይ ተዋበ፤  ምገባው በመጀመሩ ያቋረጠውን  ትምህርቱን መጀመሩን ይናገራል፡፡ ድጋፍ የሚያደርግለት ስሌለ ትምሀርቱን አቋርጦ የእለት ጉርሱን ለማሟላትም ከአቅሙ በላይ የሆነ ስራ ይሰራ እንደነበርም ነው ተማሪ ሲሳይ የገለጸው፡፡ በኒው ኤራ የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህርት የሺመቤት ደለለኝ እንደሚሉት፤  ምገባው ከመጀመሩ በፊት ምሳ  ይዘው የማይመጡ  ተማሪዎችን  በራሳቸው ወጪ ለመመገብ  ሙከራ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፤  ዛሬ ላይ  ዛላቂ መፍትሄ  በመሰጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች  ደብተር እንኳ  ለማሟላት ስለሚቸገሩ  የመማር ማስተማሩን አስቸጋሪ ያደርገው እንደነበር የገለጹት መምህርት  የሺመቤት፤ አሁን ችግሩ መቀረፉን ይናገራሉ፡፡ የአጼ ልብነ ድንግል አጸደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር  ክንድየ ወርቄ እንደሚሉት፤ የምገባ ፕሮግራሙም ሆነ ሌሎች የተደረጉ ድጋፎች  በተማሪዎች መካከል የእኩልነት መንፈስ እንዲመጣና ትምህርታቸው ላይ  እንዲያተኩሩ አስችሏል፡፡ ከዚህ በፊት በርካታ ተማሪዎች  የእለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ስራ ፍላጋ ስለሚሄዱ ትምህርታቸውን  ያቋርጡ እንደነበር  ገልጸው፤ ድጋፉ ከተጀመረ በኋላ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ መሆኑንም ተናግረዋል። ርእሰ መምህር  ክንድየ  እንደሚሉት የተጀመረው ድጋፍ ጥሩ ቢሆንም ለአንድ ተማሪ የተመደበ በጀት የወቅቱን የገበያ ዋጋ ያላገናዘበ በመሆኑ መሻሻል አለበት። የአዲስ አበባ ትምርት ቢሮ  የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው አሰራሩን ወጥ ለማድረግና  የተጠያቂነት  አሰራር ለመዘርጋት መመሪያ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም