በድሬዳዋ አስተዳደር ለ68 ሺህ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት ተሰጠ

51

ኢዜአ ታህሳስ 5/2012 የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ 68 ሺ በላይ ህፃናት ቤት ለቤት የፖሊዮ ክትባት መሰጠቱን ገለጠ፡፡ በሚቀጥለው ወርም ተጨማሪ ክትባት እንደሚሰጥ ቢሮው  አስታውቋል፡፡

በቢሮው የጤና ማበልጸግ ቡድን አስተባባሪ ሲስተር መሰሉ አጥናፌ ለኢዜአ እንደገለጡት ላለፉት አምስት ቀናት በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ ቀበሌዎች ከ68 ሺ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት ቤት ለቤት ተሰጥቷል፡፡

''ተጨማሪ ሁለት ቀናት በመመደብም በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በጎዳናዎች ያልተከተቡ ከ300 በላይ ህፃናት ተገኝተው እንዲከተቡ ተደርጓል'' ብለዋል፡፡

በንክኪ የሚተላለፈውን የፖሊዮ ቫይረስ አስቀድሞ ለመከላከልና ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በሽታን መከላከል አቅማቸው እንዲጨምር ክትባቱ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሲስትር መሰሉ ገለጣ በክትባት ዘመቻው 61 ሺ ህፃናት ለመከተብ የታቀደ ቢሆንም አዳዲስ መንደሮች መስፋፋትና አዳዲስ ህፃናት መወለዳቸው የተከተቡት ህጻናት ከ68 ሺ በላይ ሆነዋል፡፡

በዘመቻው በተለያየ የጤና ሙያ ደረጃ የሚገኙ 211 አባላት መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ህጻናቱን ለማስከተብ ያሳየው ተነሳሽነትና ግንዛቤ ለሥራው መሳካት አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

ጤና ቢሮው የህጻናቱን የበሽታ መከላከል አቅም ለማሳደግና ተደራሽ ያልሆኑ ህጻናት ጭምር ለመሸፈን በሚቀጥለው ወር ተመሣሣይ የክትባት ዘመቻ ለማከናወን ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

መምህርት ጫልቱ ከድር በትምህርት ቤቶች የተካሄደው የክትባት አሰጣጥ ስኬታማ ቢሆንም ጠረፋማና ተራራማ አካባቢ የሰፈሩ ቤተሰቦችን ዳግም መፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡

ክትባቱ ልጄ ከሚደርስበት ተላላፊ በሽታ እንደሚከላከልለት በመረዳቴ ነው ያስከተብኩት ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኮኮቤ ተሰማ ናቸው ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም