ዴንማርክ ለኢትዮጵያ ምርጫ የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ልታደርግ ነው

88
ኢዜአ 4/2012 የዴንማርክ መንግስት በ2012 ዓ.ም ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው። በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሚስ ካሪን ፖልሰን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳሌህ የድጋፍ ስምምነቱን ትናንት ተፈራርመዋል። ዴንማርክ ድጋፉን የምታደርገው መጋቢት 2011 ዓ.ም የአገሪቷ የልማት ትብብር ሚኒስትር ራስሙስ ፕሬን በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት በገቡት ቃል መሰረት መሆኑን ከዩኤንዲፒ ኢትዮጵያ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የዴንማርክ መንግስት ድጋፉ በኢትዮጵያ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት ምርጫዎችን በሚደግፍ ፕሮጀክት ላይ ለሚሰሩ ስራዎች የሚውል ነው። በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሚስ ካሪን ፖልሰን በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ አገሪቷ ወደፊት ብልጽግናና ሰላም ለማምጣት ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። ዴንማርክ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ዩኤንዲፒ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ሁለገብ ጥረትን በመቀላቀሏ ደስተኛ መሆኗን ተናግረዋል። የዩኤንዲፒ ኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳሌህ በበኩላቸው ዴንማርክ ለምርጫው ድጋፍ ለማድረግ እየሰፋና እያደገ የመጣውን የዓለም አቀፍ አጋሮች ጥምረት መቀላቀሏን ገልጸው፤ ለምርጫው ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ዴንማርክን ጨምሮ 10 የልማት አጋሮች እስካሁን በኢትዮጵያ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት ምርጫዎችን በሚደግፍ ፕሮጀክት(ሲድስ ፕሮጀክት) 40 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል መግባታቸውን  የዩኤንዲፒ ኢትዮጵያ ቢሮ መረጃ ያሳያል። እ.አ.አ ከ2019 እስከ 2022 ተግባራዊ የሚሆነው ሲድስ ፕሮጀክት በስሩ ሶስት ቁልፍ ጉዳዮችን ይዟል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ግልጽና ሁሉን አቀፍ ምርጫ በብቃት እንዲካሂድ፣ ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆንና ውጫዊ የተግባቦት ስራዎች በተደራጀ መልኩ እንዲያከናውን የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማከናወን እንዲሁም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን ቦርዱና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የመለየት፣ የመቆጣጠርና ምላሽ የመስጠት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ መደገፍ ሶስቱ የፕሮጀክቱ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከልማት አጋሮች የሚገኘውን ገንዘብ በዩኤንዲፒ ኢትዮጵያ የሚሰበሰብ ነው። ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም የፊንላንድ መንግስት በ2012 ዓ.ም ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የሚውል የ800 ሺህ ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ከዩኤንዲፒ ኢትዮጵያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም