የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከል ግንባታ ተጠናቀቀ

216
ኢዜአ ታህሳስ 4/2012 በአዲስ አበባ ያለውን የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ አቅርቦት ችግር መፍታት የሚያስችል የማምረቻ ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁ ተገለጸ። የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከእውን የበጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ የእግር ጉዞ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። "በሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ እጥረት ጉዞዬ አይገታም" በሚል መርህ ነገ የሚካሄደው የእግር ጉዞ የአካል ድጋፍ ለአካል ጉዳተኞች መሰረታዊ ስለመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚረዳ ታምኖበታል። የእውን የበጎ አድራጎት ማኅበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማርታ ደጀኔ እንደገለጹት አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ በማጣት ሊሰሯቸው ከሚፈልጓቸው ነገሮች እየተገደቡ ነው። የአካል ድጋፍ በሚቀየርበት ጊዜ ከዋጋ፣ ከጥራትና ከምቾት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ጠቁመው ተቋሙ ከበጎ ፈቃደኛ ኢንጂነሮች ጋር በመተባበር በአንድ ዓመት 15 ዊልቼሮች እንዲገጣጠሙ ማድረጉን ገልፀዋል። ይህም መግዛት የሚችሉ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙና አቅሙ የሌላቸው ደግሞ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች ከተገኙ በነፃ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ አሰፋ እንደገለጹት የአካል ድጋፍ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም፤ የአቅራቢ ድርጅቶች ቁጥርም አነስተኛ ነው። በቅርቡ የሰራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ባገኘው ድጋፍ 6 ሺህ የሚጠጉ የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች የተሰራጩ ሲሆን 300 ዊልቼሮች ለከተማዋ ለመስጠት ቃል ተገብቶ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። በከተማዋ የሚከሰተውን የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ እጥረትና ተደራሽነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሚኬሊላንድ አካባቢ የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመዋል። ተቋሙን ወደ ማምረት ለማስገባት የቁሳቁስ ግዢ መፈፀሙን ገልፀው ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ስራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል። ለተቋሙ ግንባታና ለቁሳቁስ ግዢ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ተናግረዋል። ታሕሳስ 5 ቀን 2012 ዓ.ም መነሻውን አራት ኪሎ፤ መድረሻውን ደግሞ ስድስት ኪሎ የሚያደርገው የእግር ጉዞ ተሳታፊዎች ከጠዋቱ 1 ሠዓት ከ30 እስከ 2፡00 ሠዓት መነሻው ቦታ እንዲገኙም ጥሪ ቀርቧል። በኢትዮጵያ ከሕዝቧ ቁጥር ከ17 በመቶ በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም