የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ተቋም በ200 ሚሊዮን ብር ፋብሪካ ሊያስገነባ ነው

62

ኢዜአ ታህሳስ 4 ቀን 2012 የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ተቋም ማይጨው ላይ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የፕሌይ ውድ ማምረቻ ፋብሪካ ሊያስገነባ መሆኑን አስታወቀ።

የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ተቋም /ኢፈርት/ በስሩ 16 ድርጅቶች ሲኖሩት ማይጨው ፓርቲክል ቦርድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንደኛው ነው።

ማኅበሩ ለኮርኒስ፣ ለወለል ንጣፍና ለህንጻዎች መከፋፈያ የሚያገለግሉ የፕሌይ ውድ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ የሚያቀርብ ነው።

በተጨማሪም ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስና ምርቶቹን ወደ ቻይና በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑ ተገልጿል።

ማኅበሩ ዛሬ ከምርቱ ተረካቢዎች፣ አከፋፋዮችና ተጠቃሚዎች ጋር በአዲስ አበባ ባካሄደው ምክክር በ200 ሚሊዮን ብር አዲስ የፕሌይ ውድ ማምረቻ ፋብሪካ ለማስገንባት ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ ብሏል።

በትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ተቋም የሚገነባው ፋብሪካ 40 በመቶው በቻይና ባለሃብት እንደሚከናወን ተገልጿል።

ግንባታው ተጠናቆ ስራ ሲጀምር ከ100 ሜትር ኪዩብ በላይ ፕሌይ ውድ የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ነው የተነገረው።

የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ሲነርጂና ሎካል ኢንተግሬሽን ዲቪዥን ሃላፊ አቶ ሰለሞን ደሳለኝ የፋብሪካው ግንባታ መቼ እንደሚጀመር ባይገልጹም ተጠናቆ ስራ ሲጀምር ግን ከ600 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም