በጋሞ ዞን አብዛኛው የደረሰ የመኽር ሰብል በዘመቻ ተሰበሰበ

113

ኢዜአ ታህሳስ 4 ቀን 2012 በጋሞ ዞን በ80 ሺህ 972 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የደረሰ የመኽር ሰብል መሰብሰቡን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት እንዳያስከትል አብዛኛው የደረሰ ሰብል በዘመቻ መሰብሰቡ ተናግሯል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ማቲዮስ ሙላቱ ለኢዜአ እንደገለፁት እስካሁን የተሰበሰበው ሰብል በምርት ወቅቱ ታርሶ በዘር ከተሸፈነው 96 ሺህ 646 ሄክታር ማሳ ውስጥ ነው ።

ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ በ14 ወረዳዎች እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት እንዳይደርስ አብዛኛው የደረሰ ሰብል በዘመቻ መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

አቶ ማቲዮስ እንዳሉት በሰብል ስብሰባው ተማሪዎች፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች ስር የሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች ጨምሮ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።

እየጣለ ያለው ዝናብ እስከ ታህሳስ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል የአየር ትንበያ መረጃ በማመላከቱ ከቀሪው ማሳ ላይ ሰብልን በዘመቻ የመሰብሰቡ ሂደት መቀጠሉን ጠቁመዋል ።

በዞኑ የምዕራብ ዓባያ ወረዳ አልጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካልሳ ያሱማ ከአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የደረሰ የበቆሎ ሰብል በህብረተሰብ እገዛ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል ።

የደረሱ ሰብሎችን ከሰበሰቡ በኋላ ማሳ ላይ ከምሮ የማቆየት ልምድ እንደነበራቸው የጠቀሱት አርሶ አደሩ ዘንድሮ ያልተጠበቀ ዝናብ በመጣሉ የሰበሰቡትን በቆሎ ሙሉ ለሙሉ በጎተራ መክተታቸውን ገልጸዋል ።

"ተማሪዎች ጊዜያችንን በመሰዋት የደረሰ ሰብል በዘመቻ ሰብስበናል" ያለው ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪና የ11ኛ ክፍል ተማሪ ዋፋ ሰለሞን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም