የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለፁ

50
ኢዜአ ታህሳስ 03 / 2012 ዓ.ም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተለመደ የበጎ አድራጎት ስራ ባሻገር ልማትን ከሰላም ግንባታ ሥራ ጋር በማጣመር እንደሚያከናውኑ አስታወቁ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች፤ በኢትዮጵያ ጠያቂ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚተጉ አስታውቀዋል። የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት አዛገ እንደሚናገሩት፤ የሴቶችና ህፃናት ህይወትን መሰረት ለማስያዝ የተቋቋመው ድርጅት በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ክልሎች ስራውን እያከናወነ ይገኛል። ድርጅታቸው ለሴቶችና ሕጻናት ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ ለኅብረተሰቡ እርስ በርስ ስለመፈቃቀርና መተሳሰብ እያስተማረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሰላምን ለማስፈን የሁሉም ሰው ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ለማረጋገጥም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። ''ሰላም በንግግርና በውይይትየሚሰፍን መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ተግባራዊነት ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል'' ብለዋል። የ'ላይቭ አዲስ' መስራችና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተሾመ በበኩላቸው በግጭት አፈታት ዙሪያ ወጣቱን ያማከለ ስራ ለመስራትና ወጣቱ ግዴታውን አውቆ መብቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲጠይቅ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገለጹ። በሚተገብሯቸው ስድስት ፕሮጀክቶች ሰላማዊ የሆነ ተግባቦት አንዱ መርህ ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል። በወጣቶችና ሴቶች ላይ ያተኮሩና በቅርቡ በሚተገበሩ ሁለት ፕሮጀክቶች ሰላምን የሚያውኩ ነገሮችና መፍትሄዎች ላይ ለመስራት መታቀዱን አስረድተዋል። ሁለቱ ፕሮጀክቶች ከመሰል ድርጅቶች ጋር በመተባበር በወጣቶች ተሳታፊነትና ከስደት ተመላሾችና ወደስደት ለመሄድ ባሰቡ ሰዎች ላይ የሚሰሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በደቡብ ክልል መሰረቱን ያደረገው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መረጃ ማዕከል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩሲያ በቀለ እንደገለጹት፤ ማህበሩ የሲቪክ ማህበራትን አቅም የማጎልበትና በትብብር እንዲሰሩ የማድረግ ተግባር እየከወነ ነው። ስለሰላም አበክረው ለሚሰሩ የመንግስትና የማህበረሰብ የሰላም ተዋንያን የአቅም ግንባታና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለሰላም ግንዛቤ የመስጠት ተግባር መከወናቸውን ገልጸዋል። ማህበሩ ለሰላም ተዋንያን ግጭትን በመከላከል፣ መቆጣጠርና መፍታት በተመለከተ የሚስተዋልባቸውን ክፍተት በመለየት የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ ያዳበራቸውን የግጭት አፈታት ዘዴዎች የማጠናከር ስራ ለመስራት፣ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች እንዲወያዩ መድረክ ለማመቻቸት ማቀዳቸውንም ገልፀዋል። የግጭቱ መንስኤ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ከሆነ ችግሩን ለመፍታትና ልማትንና ሰላምን አጣምሮ ለመስራት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመስራት መታሰቡን ገልፀው፤ ለዚህም ሃብት የማሰባሰብ ስራ መጀመሩንና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ተናግረዋል። ኃላፊዎቹ ሲቪክ ማህበራት ከተለመደው የእርዳታ ድጋፍ ባሻገር ወቅቱ ከሚጠይቀው ሁኔታ አኳያ ራሳቸውን በማስተካከል በአገሪቷ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ አገልግሎት ማግኘት መብት መሆኑን እንዲገነዘብና ጠያቂና ሞጋች እንዲሆን ለመስራት መታሰቡንም አስረድተዋል። የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ለአገሪቷ ልማት፣ ዲሞክራሲና የሰላም ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ኤጀንሲው ይህን አስተዋፅኦዋቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል ድጋፍ እንደሚያደርግ በመጠቆም።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም