በጌዴኦ ዞን የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት መጨመሩ ተነገረ

61
ኢዜአታህሳስ 3 / 2012 በጌዴኦ ዞን የኤች አይ ቪ / ኤድስ ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። "ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው" በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮ የዓለም ኤድስ ቀን በዞን ደረጃ ትላንት በዲላ ከተማ ተከብሯል። የዞኑ ጤና መምሪያ የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ፈይሳ በወቅቱ እንደገለጹት በዞኑ የቫይረሱ ስርጭት ቀደም ሲል ከነበረበት 1 በመቶ ወደ 3 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ብሏል። በዘርፉ ይደረግ የነበረው የመከላከል ሥራ መቀዛቀዝ፣ ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ የጫት፣ የሽሻና መጠጥ ቤቶች መስፋፋት ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር ምክንያቶች ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዞኑ የኢትዮ- ኬንያ መተላለፊያ ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የንግድ እንቅሰቃሴ መስፋፋትም ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ፍቅሩ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ተማሪዎችን የሚያዘናጉና ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ንግድ ቤቶች እየተስፋፉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ከዞንና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በዘርፉ ይሰራቸው የነበሩ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስራዎች መቀዛቀዛቸውን ጠቅሰዋል ። የበሽታውን ሰርጭ ለማስቆም ከዚህ ቀደም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በትኩረት ይሰሩ የነበሩ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል ። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነው። የዩኒቨርሲቲው ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘርፍ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ደስታ አጁላ በአንዳንድ አካባቢዎች ዛሬም እየተስተዋለ ያለው ማግለልና መድልዎን ለማስቀረት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል። በፓናል ውይይቱ ላይ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከስምምነት ተደርሷል። ቀኑ የተከበረው የዞኑ ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘርፍ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረጉት ትብብር ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም