አይኤምኤፍ እና ዳግ ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማጠናከር የሚውል 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
አይኤምኤፍ እና ዳግ ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማጠናከር የሚውል 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገብተዋል
54
ኢዜአ ታህሳስ 3/3012 ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የልማት አጋሮች ቡድን (ዳግ) ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማጠናከር የሚውል 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ አይኤምኤፍ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን እና የልማት አጋሮች ቡድን 3 ቢሊዮን በድምሩ የ5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ገንዘቡ አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማጠናከር የሚውል ነው። የልማት አጋሮች ቡድኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገሮችንን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል። ጳጉሜ 2011 ዓ.ም አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውያን አስመልክቶ ከልማት አጋሮች ጋር ውይይት መደረጉንና ስለ ማሻሻያው ገለጻ እንደተደረገላቸውም አስታውሰዋል። በውይይቱም ላይ የልማት አጋሮች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንና በዚሁ መሰረት ባለፉት ሁለት ቀናት ሁለቱ አካላት የገንዘብ ድጋፉን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል። ቃል የተገባው ገንዘብ ለሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ማለትም ለማክሮ ኢኮኖሚ፣ ለመዋቅራዊና ለሴክቶራል ማሻሻያዎች የሚውል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ''የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትና በሳውዲ ዓረቢያ የተደረጉልን ድጋፎችንም እናደንቃለን፤ ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎች ይኖሩናል ብለን እንጠብቃለን'' ማለታቸው ይታወሳል። ይህም በመንግሥት እና በድጋፍ ሰጭዎች አጋርነት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና እና ሰላማዊ አገር ለማሸጋገር ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።