የኢትዮ-ሱዳን አጎራባች ዞኖች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ

51
ኢዜአ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮ-ሱዳን አጎራባች የፈሽካ እና የምዕራባዊ ትግራይ ዞኖች ነዋሪዎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማሳደግ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የየዞኖቹ አመራሮች ተወያዩ። በፈሽካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የተመራ የልዑካን ቡድን በሰቲት ሁመራ ከተማ ባደረገው የሁለት ቀን ጉብኝት ማጠናቀቂያ ላይ ከምዕራባዊ ትግራይ ዞን አመራሮች ጋር በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣በህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ቁጥጥርና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት መክረዋል። በመድረኩ ላይ የፈሸካ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሳድቅ ካሊድ ኢትዮጵያ ለሱዳናዊያን ቤታቸው እንደሆነች ገልጸው ሁመራ በርካታ ዜጎቻቸው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል ። ትላንት ማታ የተጠናቀቀው ጉብኝትም የሁለቱን ህዝቦች ወዳጅነት የሚያጠናክረው መሆኑን አስታውቀው በቆይታቸው ለተደረገላቸው እንክበካቤ ምስጋና አቅርበዋል ። የትግራይ ምዕራባዊ ዞን የልዑካን ቡድን ከሶስት ቀን በፊት በፈሽካ ዞን ተመሳሳይ ጉብኝት ማድረጉን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው ናቸው ። በሁለቱም ሀገራት ተጎራባች አከባቢዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኝነት ከማጠናከር ባለፈ በጸጥታ፣በሰላም በንግድ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም አስተዳዳሪው ተናግረዋል። በድንበር አከባቢ አልፎ አልፎ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ ህገ-ወጥ የሰዎችና፣ የጦር መሳርያ ዝውውር ለመቆጣጠር በጋራ በሚሰሩበት ጉዳይ ላይም መምከራቸውም ጠቁመዋል። የአጎራባች አከባቢዎችን ሰላም ከማረጋገጥ አኳያም የሁለቱ ሀገራት አርሶ አደሮች የሚመሰገን ስራ መስራታቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ፀጥታ ኃላፊ አቶ ጊደይ አዘናው ናቸው። በዚህም ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረ ህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር የመሳሪያ ዝውውር በአሁኑ ወቅት መቀነሱን ተናግረዋል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በባህል፣ በስፖርትና በክረምት የችግኝ ተከላ በጋራ ለማጠናከር የመከሩት አመራሮቹ በመጪው የካቲት ወር በፈሸካ ከተማ ስራቸውን በጋራ ለመገምገም ቀጠሮ ይዘዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም