ሙስናን ለመከላከል ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ተጠቆመ

80
ኢዜአ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በወጣቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ተጠቆመ። በጎንደር ከተማ የመንግስት ሰራተኞችና ነዋሪዎች  የፀረ-ሙስና ቀንን አስመልክቶ  የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡ ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ሀብታሙ አድጎ  እንዳሉት  ሙስናን  በሀገሪቱ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ ወጣቶችን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ሊኖር ይገባል፡፡ አሁን በሀገሪቱ ባለው ተጨባጭ ለውጥ የወጣቱ ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወጣቶች ሙስናን መከላከል እንዲያስችላቸው ከፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር ሆነው የሚሰሩበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው አቶ ዘመነ ሀብቱ " የወጣት አደረጃጀቶችን በመጠቀም በስነ ምግባር ዙሪያ በቂ ስልጠና በመስጠትና ሙስናን መከላከል የሚያስችላቸውን አቅም ለመፍጠር መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡ ወጣቱን በማሰለፍ ሙስናን መከላከል ከተቻለ ብልሹ አሰራርን ማስወገድ እንደሚቻል አመልክተው፤ የፍትህ አካሉና ኮሚሽኑ ወጣቱን ያካተተ ስራ መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ "የነገ ሀገር ተረካቢ ለሆኑ ህፃናት በየትምህርት ቤቱ ስለሙስና አስከፊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ለቀጣይ በስነ-ምግባሩ ምስጉን ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል "ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አስካል ፍሬው ናቸው፡፡ ሙስናን ለመከላከል በስነ ምግባሩ ምስጉን የሆነ ዜጋ ማፍራት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። በክልሉ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስማማው ደሳለኝ በበኩላቸው ማንኛውም ዜጋ ሙስናን የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል። በቀጣይ ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ ወጣቶች ሙስናን ከመከላከልና ከመታገል ባለፈ ራሳቸውንም ከብልሹ አሰራር ነፃ አድርገው እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጎንደር ቅርንጫፍ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ በምክክር መድረኩ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ሌሎችም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም