ለኢ-መደበኛ የንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጡ መስሪያ ቦታዎች የከተማዋን ውበት በማገናዘብ እንዳልሆነ ተገለጸ

80

ታህሳስ 3/2012 በአዲስ አበባ ከተማ በኢ-መደበኛ ንግድ ለሚሰማሩ ማህበረሰብ አባላት የሚመቻቹ መስሪያ ቦታዎች የከተማዋን ስነ-ውበታዊ ገጽታ ታሳቢ በማገናዘብ እንዳልሆነ ተገለጸ። ኢ-መደበኛ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በከተማ አስተዳደሩ ቋሚ ቦታ ሳይሰጠው በጊዜያዊ የንግድ ፈቃድና መለያ ባጅ ብቻ በተመረጡ ቦታዎች እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው ነጋዴዎች ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ በየጎዳናው የንግድ ስርዓትን ባልተከተለ የሚሰሩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ስርዓት ለማስያዝ የራሱን ፖሊሲ፣ መመሪያና ደንብ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ በንግድ ዘርፍ የስራ ዕድልን ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

ነገር በጎዳናዎች ላይ ለኢ-መደበኛ ንግድ ተብለው የሚሰጡ ስፍራዎች በከተማ ሥነ-ውበታዊ ገጽታ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከግምት ገብቶ መሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በዚህ ወቅት በከተማዋ የንግድ ስርዓትና ስነ-ውበታዊ ገጽታ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች እንዳሉት፤ ለከተማዋ ሀብት ከንግዱ የሚገኝ ገቢ ብቻ ሳይሆን ውበቷም እንደሆነ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጭዎቹ በየመንገዱ በሚወጠሩ ሸራዎች የከተማዋን ውበት እየደበቁና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መምጣቱን አመልክተዋል።

አቶ አሸናፊ ሙሴ የተባሉ አስተያየት ሰጪ እንደገለጹት፤ ለስራ ፈጠራ እየተባለ በጎዳናዎችና አዳባባይ ዙሪያ የሚሰጡ የንግድ መስሪያ ቦታዎች የከተማውን ውበት ጥያቄ ውስጥ እየከተተው መጥቷል።

ስለሆነም ንግዱን ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ውበትም እንደሀብት ታይቶ ከንግዱ ባሻገር ሌሎች የስራ ዕድል መፍጠሪያ መስኮችን መካተት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው በንግድ ዘርፍ ላይ ብቻ መወሰን እንደሌለበትም አመልክተዋል።

በመሆኑም የከተማዋን ውበት እያጠፋ የመጣውን ኢ-መደበኛ ንግድ በጥልቀት በማየት መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች በፍጥነት ሊስተካከሉ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን አስረድተዋል።

ሌሎች ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎችም የአቶ አሸናፊን ሃሳብ ተጋርተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የንግድና ምዝገባ ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ተገኝ በበኩላቸው ቢሮው የንግድ ስፍራዎችን እየሰጠ ቢሆንም ብዙዎቹ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ፈቃድ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

የከተማ ውበትና ገጽታዎችን የሚያበላሹ ሸራዎችን የሚጠቀሙት ሳይፈቀድላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በመሆኑም ቢሮው የከተማዋን ስነ-ውበት ለማስጠበቅ ሸራዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን የማፍረስ ርምጃዎችን ቢወስድም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት “የከተማዋን ውበት በጠበቀ ንግዶችን እንዴት ማዘመንይቻላል?” በሚል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ የከተማዋን ውበት ያስጠበቀ የንግድ ስርዓትን ለመተግበር የሚያስችል የቦታ ልየታና ዲዛይን ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም